Tuesday, February 28, 2017

በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት በብዙ ቦታዎች የተጠቀሰው የጌታ መልአክ ማነው???

ጳውሎስ ፈቃዱ እንደጻፈው

 “ያሕዌ” እና “የያሕዌ መልአክ”
ከእግዚአብሔር ወልድ የዘላለም ልጅነት ጋር የሚጣጣሙ ማስረጃዎች በብሉይ ኪዳንም አሉ። ለምሳሌ እግዚአብሔር በሚነድድ ቊጥቋጦ መካከል ለሙሴ የተገለጠበትን መንገድ ማጤን ይቻላል (ዘፀ. 3፥1 - 4፥17)። ታሪኩ ሲጀምር ለሙሴ የተገለጠው አካል፣ “የእግዚአብሔር መልአክ” ተብሎ ነው የተዋወቀው (3፥2)። ከዚያ በኋላ ግን፣ በታሪኩ ውስጥ “የእግዚአብሔር መልአክ” መባሉ ቀርቶ “እግዚአብሔር” እየተባለ ነው የቀረበው (3፥4፡6፡7፤ 4፥2፡4፡5፡6፡10፡11፡14)። ሙሴም የሚያነጋረውን አካል ስም ሲጠይቅ፣ “ያለና የሚኖር” ወይም “ያህዌ (יהוה)” የሚል ምላሽ አግኝቷል (3፥14)። ተናጋሪው አካል፣ “እኔ የአባትህ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ” በማለት ራሱን ለሙሴ አስተዋውቋል (3፥6፡15)። በተጨማሪም በንግግሩ ውስጥ ሁሉ፣ “የሕዝቤን ጩኸት ሰማሁ፤ መከራቸውን አየሁ፤ አድናቸዋለሁ፤ ከግብፅ አወጣቸዋለሁ፤ አንተንም እልክሃለሁ፤ ወዘተ.” በማለት የአንደኛ መደብ ቋንቋን ነው የሚጠቀመው። እሳት ከእግዚአብሔር መገለጥ ጋር እንደሚያያዝም ይታወቃል (ዘፀ. 13፥21-22፤ 19፥18፤ 40፥38፤ 1ነገ. 18፥24፡38)። ታዲያ ይህ መልአክ ማነው?   

ለያዕቆብ የተገለጠለትም “መልአክ” ራሱን “የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ” በሚል ነው የገለጠው (ዘፍ. 31፥11-13)። በሌላ ስፍራ ደግሞ፣ ኀጢአትን  ይቅር የማለትና ያለ ማለት ሥልጣን ያለው ሆኖ ቀርቧል (ዘፀ. 23፥20-21)። እስራኤላውያንን ከግብፅ ያወጣው እርሱ መሆኑን፣ ከእነርሱም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንደሚጠብቅ፣ እነርሱ ግን የገቡለትን ቃል ባለመጠበቃቸው ማዘኑንም ይናገራል (መሳ. 2፥1-3)። ለጌዴዎን ሲገለጥም (መሳ. 6፥11-24)፣ “የእግዚአብሔር መልአክ” (ቊ. 11፡12፡20፡21) እና “እግዚአብሔር” (ቊ. 14፡16፡20) እየተባለ ተጠርቷል። በዘካርያስ 12፥8ም በዚሁ መልክ ተጠቅሷል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በዚህ መልኩ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ሆኖ የተገለጠ መልአክ የለም።[36] ለምን?

ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት፣ “መልአክ” ከሚለው ቃል ትርጓሜ መጀመር ግድ ይሆናል። መልአክ በዕብራይስጥ ማላክמַלְאָך) ) ሲሆን፣ መልአክ፣ መልእክተኛ፣ ልዑክ የሚሉ ትርጓሜዎችን ይዟል።[37] (የሚገርመው ነገር በግሪኩም ትርጓሜው ይኸው መሆኑ ነው![38]) ለምሳሌ፣ በምሳሌ 17፥11 የሚገኘውን ይህንኑ “ማላክ” የተሰኘ ቃል፣ የ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ “መልአክ” ሲለው፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም እና የ1997 ትርጕም “መልእከተኛ” ብለውታል። በ2ኛ ነገሥት 1፥3 ውስጥ 2 ጊዜ የሚገኘው ይኸው ቃል፣ በዚያው ጥቅስ ውስጥ “መልአክ” እና “መልእክተኞች” ተብሎ ነው የተተረጐመው። በዕብራይስጡ “ማላከ ሞት” (מַלְאָךְ מָוֶת) የሚለው ስያሜ “የሞት መልእክተኛ” (ምሳሌ 16፥14)፣ “ማልአክ ሻሎውም” (מַלְאָךְ שָׁלֹום) ደግሞ “የሰላም መልእክተኞች” (ኢሳ. 33፥7) ተብሏል።[39] ማላክ የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ውስጥ 213 ጊዜ ሲገኝ፣ ለምሳሌ NIV መጽሐፍ ቅዱስ፣ 108 ጊዜ መልአክ/መላእክት፣ 83 ጊዜ መልእክተኛ/መልእክተኞች፣ 8 ጊዜ ደግሞ ልዑክ/ልዑካን (envoy, delegation, official) በማለት ተርጕሞታል።[40]

ስለዚህ ይህ “የቤቴል አምላክ”፣ “የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ” የሆነውና “ያሕዌ ነኝ” ያለው “መልአክ” በእርግጥም ያህዌ መሆኑ እንደማያጠራጥር ሁሉ፣ መልእክተኛ (የተላከ) መሆኑም አያጠራጥርም። ይህ ደግሞ አስቀድመን ካነሣነው ሐሳብ ጋር ይገጥማል። እግዚአብሔር ወልድ፣ የእግዚአብሔር አብ ልጅ የሆነው ከዘላለምም ነውና በብሉይ ኪዳን የአባቱ መልእከተኛ በመሆን (እየተላከ) ይመጣ እንደ ነበር መናገር ይቻላል። እርሱ ያሕዌም፣ የያሕዌ መልእክተኛም ነው። አብ በአባትነቱ ወልድን ይልካል፤ ወልድም በልጅነቱ ለአብ ይላካል! የእግዚአብሔር መልአክ የተሰኘው፣ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት (ቅድመ ትስጉት) የተገለጠበት መገለጫ ማንነቱ ነበር። ከሙሴ በፊት፣ ለአብርሃምም፣ ለአጋርም፣ ለያዕቆብም የተገለጠው ያ እግዚአብሔር ወልድ ነው።

No comments:

Post a Comment