Saturday, February 22, 2014

የኢየሱስ ዘር ሐረግ በማቴዎስና በሉቃስ ወንጌል ለምን ተለያየ?

አንድ ኦርቶዶክስ ወንድም የማቴዎስንና የሉቃስ ወንጌል ላይ የተዘረዘሩትን የኢየሱስ የዘር ሐረግ አንስቶ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጴንጤዎች ይመልሱልኝ ብሎ ጠየቀ

1. ስንት ኢየሱሶች ተወልደውልናል? ምናልባት እናንተ ሁለት አድርጋችሁ ስለምታመልኩ የትኛው ኢየሱስ ነው አምላክ የትኛው ነው አማላጅ (በማንኛቸው ታሪክ የተጠቀሰው? ማለት) ? ወይንስ ትውፊትን መቀበል ግድ ይሆናል ? 


2. ድንግል ማርያምና ዮሴፍ ምን ግንኙነት ስላላቸው የጌታ የዘር ሐረግን በዮሴፍ በኩል አድርገው ሁለቱም ቆጠሩ? 


3. አንዳንዶች ያዋየሁዋቸው ብልሆችም እገሌ የማርያምን እገሌ ደግሞ የዮሴፍን ለማለት ሞክረዋልና በዚህ መንገድ የምትሄዱም ካላችሁ 66 መጽሐፍት ማስረጃችሁን አስነብቡኝ


ለመማማር ስለሆነ መልሳችሁ በሙሉ ያለነቀፋና ያለማመጠጋጋት በማስረጃ ቢሆን ይመረጣል ማንን እንደምታመልኩ አለማወቃችሁን መመስከርም መልስ ይሆናልና ድፍረቱ ይኑራችሁ። 

እንግዲህ መልሴ ይኸው….

መጀመርያ ለጠየቀው
ስንት ኢየሱሶች ተወልደውልናል? ምናልባት እናንተ ሁለት አድርጋችሁ ስለምታመልኩ የትኛው ኢየሱስ ነው አምላክ የትኛው ነው አማላጅ (በማንኛቸው ታሪክ የተጠቀሰው? ማለት) ? ወይንስ ትውፊትን መቀበል ግድ ይሆናል ? 

የኔ መልስ...
ይህ እንግዲህ በሕልሙ ካልሆነ በስተቀር አንድም ክርስትያን ሁለት ኢየሱስ ብሎ አያመልክም ስለዚህ ይህን እንደቁምነገር ሳይሆን እንደፌዝ አየዋለሁ:: እኛ የምናመልከው አምላክ የሆነው ሰውን ሊያድን ከድንግል ማርያም የተወለደውን ኢየሱስን ነው በእዚህ ምድር ሲመላለስም ፍፁም አምላክ አንዲሁም ፍፁም ሰው ነበር

ሁለተኛ ሶስተኛ ለጠየቀው
2. ድንግል ማርያምና ዮሴፍ ምን ግንኙነት ስላላቸው የጌታ የዘር ሐረግን በዮሴፍ በኩል አድርገው ሁለቱም ቆጠሩ? 

3. አንዳንዶች ያዋየሁዋቸው ብልሆችም እገሌ የማርያምን እገሌ ደግሞ የዮሴፍን ለማለት ሞክረዋልና በዚህ መንገድ የምትሄዱም ካላችሁ 66 መጽሐፍት ማስረጃችሁን አስነብቡኝ

እዚህ ጋር ልብ ያላለው ነገር አለ ወንድሜ ምክንያቱም ሁለቱም ላይ ያለው የዘር ሐረግ በዮሴፍ በኩል ሳይሆን የማቴዎሱ በዮሴፍ በኩል ሲሆን የሉቃስ ደግሞ በማርያም በኩል ነው ይህ እንዴት እንደሆነ ላስረዳ

የኔ መልስ...
የማቴዎስ ወንጌል ስለክርስቶስ ሲፅፍ ለእስራኤል ሕዘብ የሚመጣውን መሲህ እየፃፈላቸው ስለነበር የኢየሱስን የዘር ሐረግ ሲጀምር የፃፈው የእስራኤል አባት ተብሎ በሚጠራው በአብራሃም ነው የጀመረላቸው ሲቀጥልም በዳዊት በኩል ቀጥሎም በሰለሞን በኩል ነው እያለ በመጨረሻም ለኢየሱስ በሕግ በኩል አባቱ በሆነው በዮሴፍ ነው የጨረሰው:: 

እዚህ ጋር ልብ ልንል የሚያስፈልገው እግዝአብሔር በሰጠው ተስፋ መሰረት በዳዊት ወንበር ላይ ለመቀመጥ የይሁዳ ዘር እንዲሁም ሕጋዊ አግባብ ያለው መሆን አለበት ስለዚህ ኢየሱስ በዮሴፍ በኩል የይሁዳ ዘር ነው እንዲሁም ከዳዊት በሁዋላ ንግስናዋ በተላለፈው በሰለሞን በኩል ነው የዘር ሐረጉ 

በእዚያ ላይ ማቴዎስ 1 ላይ ስናይ የሚናገረው የኢየሱስን ታሪክ በዮሴፍ በኩል ነው ዮሴፍ ምን ሊያረግ እንዳሰበ ምን እንዳደረገ ነው የሚናገረው 

እዚህ ላይ አንድ ነገር ለመጨመር ያህል በእዚህ በዮሴፍ በኩል ባለው የኢየሱስ የዘር ሐረግ ውስጥኢኮንያንየሚባል ሰው አለ ይህ ሰው ደግሞ እግዝአብሔርን በማሳዘኑ እግዝአብሔር እንዲህ ብሎ ረግሞት ነበር 
ኤር 22:24-30 
24 እኔ ሕያው ነኝና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ ማኅተም ቢሆን ኖሮ እንኳ፥ ከዚያ እነቅልህ ነበር፥ ይላል እግዚአብሔር

25 ነፍስህንም ለሚሹት ለምትፈራቸውም እጅ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ለከለዳውያንም እጅ እሰጥሃለሁ።

26 አንተንም የወለደችህንም እናትህን ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ አገር እጥላችኋለሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ።

27 ይመለሱባትም ዘንድ ነፍሳቸው ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አይመለሱም።

28 በውኑ ይህ ሰው ኢኮንያን የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ ነውን? ወይስ እርሱ ለአንዳች የማይረባ የሸክላ ዕቃ ነውን? እርሱና ዘሩስ በማያውቋት ምድር ስለ ምን ተጥለው ወደቁ?

29 ምድር ሆይ፥ ምድር ሆይ፥ ምድር ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ።

30 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከዚህ ሰው ዘር የሚከናወን በዳዊትም ዙፋን ላይ የሚቀመት በይሁዳም የሚነግሥ እንግዲህ አይገኝምና። መካን በዘመኑም የማይከናወንለት ሰው ብላችሁ ጻፉ።


ስለዚህ ከእዚህ ከኢኮንያን የደም ሐረግ የሚወለድ ማንኛውም ዘር በዳዊት ዙፋን ላይ እንዳይቀመጥ እግዝአብሔር ረግምዋል:: ይህ የዘር ሐረግ ደግሞ ወደሁዋላ ሲሄድ ከዳዊት በሁዋላ የንግስና መንገዱ የሄደው በሰለሞን በኩል ሲሆን እያለ ሲቀጥልም ኢያኮን ጋር ይደርሳል ስለዚህ ምንም እንኳ በደም ዘር ሐረግ የእዚህ ዘር ቢረገምም በሕግ ግን መብት ያለው የእዚህ ዘር ሐረግ ነው

ወደሉቃስ3 ስንመጣ ደግሞ የዘረ ሐረጉ የሚጀምረው እግዝአብሔር ብሎ አዳም ሲሆን ይህ ደግሞ የሰው ልጅ መሆኑን ሲሆን ሉቃስ 3 ደግሞ ሰናነብ የሚናገረው የዮሴፍ ልጅ ብሎ ሳይሆንእንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅብሎ ሲሆን የሉቃስን ወንጌል 1 ጀምሮ ስናይ ደግሞ የኢየሱስን ታሪክ በማርያም በኩል ያለውን ነው የሚነግረን ስለዚህ ይህ የኢየሱስ የዘር ሐረግ በማርያም በኩል መሆኑ ግልፅ ነው

ሌላው ቅድም በዮሴፍ በኩል እንዳለው የዘር ሐረግ ልብ ማለት ያለብን ብዬ እንደተናገርኩት አሁንም ልብ ማለት ያለብን በእዚህ የዘር ሐረግ ከዳዊት ቀጥሎ በሰለሞን በኩል ሳይሆን የዘር ሐረጉ በናታን በኩል ነው ይህ የሆነበት ምክንያት ምንም እንኳ በእዚህ የዘር ሐረግ ኢየሱስ ለዳዊት ዘር የሕግ አግባብ ባይኖረውን በደም ግኑኝነት በኩል ግን የዳዊት ዙፋንን ለማግኘት መብት አለው

ለማጠቃለል በዮሴፍ በኩል የዳዊት ዙፋን ላይ ለመቀመጥ በሕግ መብት ሲኖረው ነገር ግን በደም ዘር ሐረግ የዳዊት ዙፋን አይገባውም

በማርያም በኩል የዳዊት ዙፋን ላይ ለመቀመጥ በሕግ መብት ባይኖረውም ነገር ግን በደም ዘር ሐረግ የፋዊት ዙፋን ይገባዋል 

ስለዚህ ኢየሱስ በዮሴፍ በኩል ባገኘው የሕግ መብት እንዲሁም ደግሞ በማርያም በኩል ባገኘው የደም ዘር ግኑኝነት በዳዊት ዙፋን ላይ ለመቀመጥ ትክክለኛው ሰው ነው

መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተፃፈ ነገር ዝም ብሎ ያለምክንያት አይፃፍም በሁለቱ ወንጌሎች የተለያየ የዘር ሐረግ የተፃፈበት ትልቁ ምክንያት ይህ ነው

No comments:

Post a Comment