Monday, July 17, 2017

Universalism ሰዎች ሁሉ ከሞት በሁዋላም ቢሆን ይድናሉ የሚለው የሐሰት አስተምህሮ

መፅሐፍ ቅዱስ በደንብ ካጠናነው ሁሉም ሰዎች ይድናሉ ወደሚል ድምዳሜ አያደርሰንም:: ቃሉ የሚለውን አጠቃላይ ሐሳቡን ካልተረዳን: ወደስሕተት የምንገባ ይመስለኛል:: እስቲ ቃሉ የሚለውን እንይ

የሚድኑት...
1. የተመረጡት
**ማቴ 24:31 "መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።"
**2 ቲሞ 2:10, 19 "ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ።...19 ሆኖም፦ ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም፦ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል።"
**ቲቶ 1:1-2 "የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥"

2. የተዘጋጁ...
**የሐዋ ሥራ 13:48 "አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤

3. ሰምተው የዳኑ...
**ዮሐ 5:24 "እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።"
**ኤፌ 1:13 "
እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤"

4. ያመኑ...
**ዮሐ 1:11-13 "የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።"
**ዮሐ 3:16.18.36 "በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።..18በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።.. 36በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።"
**ዮሐ 11:25-26 "ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።"

እንዲህ እንዲህ እያልን ከጠቀስኩት በተጨማሪ ብዙ ማስረጃዎች ሰዎች በሕይወት እያሉ በክርስቶስ ካመኑ እንደሚድኑ ማስረጃዎችን መጥቀስ ሲቻል በተቃራኒው ደግሞ እንደቃሉ ያልኖሩ የሚደርስባቸውን ጥፋትና ፍርድ መጥቀስ እንችላለን

የሚጠፉት...
**ማቴ 7:21 "በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።"

**ማር 10:45 "እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።"
#ብዙዎች ማለት ሁሉም ማለት አይደለም!

**ማር 3:28-29 "
እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤
በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።

**ዳን 12:2 "በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።"

**ማቴ 18:9 "ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።"

**ዮሐ 5:28-29 "
በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።"

**ይሁዳ 7 "እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።"

**2 ተሰ 1:8-10 "እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።"

**ማቴ 25:41 "በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።"


**ማር 14:21 "የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው።"

ከብዙ በጥቂቱ ያላመኑ ሰዎች የሚደርስባቸውን የዘላለም ጥፋት ካየን በሁዋላ ይህን ጥቅስ ማየት ነገሮችን ሊያጠቃልልልን ይችላል

**ዕብ 9:27 "ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥"

እንግዲህ ከላይ ያልኩትን ካልኩኝ በሁዋላ የዩንቨርሳሊዝም እምነት ተከታዮች ሁሉም ሰው ይድናል ብለው በሰፊው የሚጠቅሱትን ጥቅሶች እንይ

1. 1 ጢሞ. 2:3-4 "ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።"

2. 2 ጴጥ. 3:9 "ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።"

ስለነዚህ ጥቅሶች የተረዳሁትን ከማካፈሌ በፊት ይህን ጥቅስ እንይ ማቴ. 25:46 "እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።" እዚህ ጥቅስ ላይ ሁለት በግሪኩም አንድ የሆኑ "ዘላለም" በግሪኩ "aionion" የሆነ ቃል አለ በግልፅ እንደተቀመጠው አምነው የፀደቁ የዘላለም ሕይወት እንዳገኙ ሲናገር በተቃራኒው ደግሞ ያላመኑ የዘላለም ቅጣት እንደሚደርስባቸው ይናገራል

እዚህ ጋር የዩንቨርሳሊዝም ተከታዮች ፃድቃን የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ ሲያምኑ ሃጥያአንን በተመለከተ ዘላለም የሚለውን ለተወሰነ ጊዜ እንጂ ለማያልቅ ጊዜ አይደለም ይላሉ ምንም እንኳ በግሪኩም ቢሆን ዘላለም የሚለው ቃል ለሁለቱም አንድ አይነት ቢሆንም

እንዲሁም በተመሳሳይ በ2 ጢሞ 4:18 "ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።" በሚለው ቃሉ ላይ "ከዘላለም እስከ ዘላለም" የሚለው የጊዜ ወሰን የሌለው መጨረሻ የሌለው ክብር ለእግዝአብሔር ይሁን ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለ ሲቀበሉ በተቃራኒው ደግሞ በገሪኩም ተመሳሳይ ቃላት እዚህ ቃል ላይ ... ራዕ. 20:10 "ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።" .... "ከዘላለም እስከ ዘላለም"ሲል የጊዜ ወሰን አለው መጨረሻ አለው ብለው የቃሉን ትርጉም ይለውጡታል ምንም እንኳ ሁለቱም ቦታ የግሪኩ ቃል ተመሳሳይ eis tous aionos ton aionon ቢሆንም

አሁን ከላይ ወደጠቀስኩት ጥቅሶች ስመለስ...1 ጢሞ. 2:3-4 ... ጥቅሱን ስንረዳ እግዝአብሔር ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ እንዲደርሱ ይወዳል ነገር ግን እሱ ይህን ቢወድም ሰዎች ሁሉ ግን እሱ ወዳሰበላቸው አይደርሱም ለምሳሌ እግዝአብሔር ሰዎች ሃጥያአትን እንዲሰሩ አይፈልግም አይወድም ሰዎች ግን በራሳቸው ፈቃድ ሃጥያአትን ይሰራሉ ስለዚህ እግዝአብሔር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ቢወድም በሰዎች ምርጫ የተነሳ ሰዎች ሁሉ አይድኑም በሕዝቂየል 33 11 እንዲህ ይላል ..."እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።"

በሌላም ቦታም እግዝአብሔር እንዲህ ይላል...ዮሐ 3:36 "በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።" ስለዚህ እግዝአብሔር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ወደእውነትም እንዲደርሱ ይወዳል እንጂ ከሰዎች ምርጫ የተነሳ ሰዎች ሁሉ አይድኑም ከአጠቃላይ የእግዝአብሔር ቃልና ሃሳብ ስንረዳ!

ወደሁለተኛው ጥቅስ ወደ 2 ጴጥ. 3:9 ስንሄድ ደግሞ እንዲሁ እንደመጀመርያው ተመሳሳይ መልስ ነው ያለው .. ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ጊዜ በመስጠት እግዝአብሔር ይታገሳል ነገር ግን እሱ ያን ሁሉ ቢታገስም ከክፉ መንገዳቸው ያልተመለሱ ሰዎች ወደዘላለም ጥፋት ይሄዳሉ

ሌላው ብዙ ጊዜ ዩንቨርሳሊስቶች ወደሚጠቅሱት ጥቅስ ስንሄድ....1 ጢሞ. 4:10 "ይህን ለማግኘት እንደክማለንና፥ ስለዚህም እንሰደባለን፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው።"... አሁንም ይህን ጥቅስ ስናይ ከእዚህ ጥቅስ ተመሳሳይ የሆነውን ዩሐ 3 16 ስናይ..."በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።"... የእግዝአብሔር ዓላማ ዓለሙን ሁሉ ወይም ሰውን ሁሉ ማዳን ነው የሚወደው የሚፈልገውም ይህንን ነው ነገር ግን አሁንም ቃሉ እንደሚለን..." ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።
በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።"... ከቃሉ እንደምንረዳው እግዝአብሔር ሰዎችን ሁሉ ለማዳን ቢወድም ያላመኑት ግን የሚጠብቃቸው የዘላለም ፍርድ ነው

ለማጠቃለል ሰዎች ሁሉ ይድናሉ ከሞት በሁዋላም የሚለው የዩንቨርሳሊዝም አስተምሮ ለምን አደገኛ እንደሆነ ልናገር...

የእዚህ እምነት አስተምሮ ተከታዮች ብዙዎቹ በድነት (Salvation) ውስጥ ባይሆኑም ወይም እንደቃሉ ባይኖሩም ብዙም አይገዳቸውም ምክንያቱም ከሞት በሁዋላም ንሰሐ የሚገቡበት እድል እንዳላቸው የእዚህ እምነት አስተምህሮን ስለሚነግራቸው ስለዚህ እንደቃሉ ለመኖር አይጨንቃቸውም ቃሉም አለመታዘዝ ብዙም አያስጨንቃቸውም ለሚያደርጉት እያንዳንዱ ነገር ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው እንዲሁም በጊዜው ተናዘው መመለስ እንዳለባቸው ብዙም አይጨነቁበትም ምክንያቱም ከሞት በሁዋላ ሁለተኛ ዕድል አላችሁ ብሎ ዩንቨርሳሊዝም ስለሚያስተምራቸው

ሰይጣን የለም ብለው ስለሚክዱም የሰይጣንን አሰራርን አይረዱትም በእሱም የሐሰት አስተምህሮ ምክንያት የኢየሱስን አምላክነት ይክዳሉ የመንፈስ ቅዱስ አምላክነት ይክዳሉ ከእዚህም የተነሳ የመንፈስ ቅዱስን አብርሆነት ያጣሉ ቃሉን በትክክል አይረዱትም

ቃሉ ስለድነት ሲናገር እንዲህ ይላል...
**2 ቆሮ. 6:2 "በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።"... የመዳን ቀን ዛሬ ነው ከሞት በሁዋላ አይደለም
**ዕብ. 4:7 "ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፦ ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል።“Today,” saying through David after so long a time just as has been said before, “Today if you hear His voice, Do not harden your hearts"

Tuesday, February 28, 2017

በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት በብዙ ቦታዎች የተጠቀሰው የጌታ መልአክ ማነው???

ጳውሎስ ፈቃዱ እንደጻፈው

 “ያሕዌ” እና “የያሕዌ መልአክ”
ከእግዚአብሔር ወልድ የዘላለም ልጅነት ጋር የሚጣጣሙ ማስረጃዎች በብሉይ ኪዳንም አሉ። ለምሳሌ እግዚአብሔር በሚነድድ ቊጥቋጦ መካከል ለሙሴ የተገለጠበትን መንገድ ማጤን ይቻላል (ዘፀ. 3፥1 - 4፥17)። ታሪኩ ሲጀምር ለሙሴ የተገለጠው አካል፣ “የእግዚአብሔር መልአክ” ተብሎ ነው የተዋወቀው (3፥2)። ከዚያ በኋላ ግን፣ በታሪኩ ውስጥ “የእግዚአብሔር መልአክ” መባሉ ቀርቶ “እግዚአብሔር” እየተባለ ነው የቀረበው (3፥4፡6፡7፤ 4፥2፡4፡5፡6፡10፡11፡14)። ሙሴም የሚያነጋረውን አካል ስም ሲጠይቅ፣ “ያለና የሚኖር” ወይም “ያህዌ (יהוה)” የሚል ምላሽ አግኝቷል (3፥14)። ተናጋሪው አካል፣ “እኔ የአባትህ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ” በማለት ራሱን ለሙሴ አስተዋውቋል (3፥6፡15)። በተጨማሪም በንግግሩ ውስጥ ሁሉ፣ “የሕዝቤን ጩኸት ሰማሁ፤ መከራቸውን አየሁ፤ አድናቸዋለሁ፤ ከግብፅ አወጣቸዋለሁ፤ አንተንም እልክሃለሁ፤ ወዘተ.” በማለት የአንደኛ መደብ ቋንቋን ነው የሚጠቀመው። እሳት ከእግዚአብሔር መገለጥ ጋር እንደሚያያዝም ይታወቃል (ዘፀ. 13፥21-22፤ 19፥18፤ 40፥38፤ 1ነገ. 18፥24፡38)። ታዲያ ይህ መልአክ ማነው?   

ለያዕቆብ የተገለጠለትም “መልአክ” ራሱን “የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ” በሚል ነው የገለጠው (ዘፍ. 31፥11-13)። በሌላ ስፍራ ደግሞ፣ ኀጢአትን  ይቅር የማለትና ያለ ማለት ሥልጣን ያለው ሆኖ ቀርቧል (ዘፀ. 23፥20-21)። እስራኤላውያንን ከግብፅ ያወጣው እርሱ መሆኑን፣ ከእነርሱም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንደሚጠብቅ፣ እነርሱ ግን የገቡለትን ቃል ባለመጠበቃቸው ማዘኑንም ይናገራል (መሳ. 2፥1-3)። ለጌዴዎን ሲገለጥም (መሳ. 6፥11-24)፣ “የእግዚአብሔር መልአክ” (ቊ. 11፡12፡20፡21) እና “እግዚአብሔር” (ቊ. 14፡16፡20) እየተባለ ተጠርቷል። በዘካርያስ 12፥8ም በዚሁ መልክ ተጠቅሷል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በዚህ መልኩ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ሆኖ የተገለጠ መልአክ የለም።[36] ለምን?

ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት፣ “መልአክ” ከሚለው ቃል ትርጓሜ መጀመር ግድ ይሆናል። መልአክ በዕብራይስጥ ማላክמַלְאָך) ) ሲሆን፣ መልአክ፣ መልእክተኛ፣ ልዑክ የሚሉ ትርጓሜዎችን ይዟል።[37] (የሚገርመው ነገር በግሪኩም ትርጓሜው ይኸው መሆኑ ነው![38]) ለምሳሌ፣ በምሳሌ 17፥11 የሚገኘውን ይህንኑ “ማላክ” የተሰኘ ቃል፣ የ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ “መልአክ” ሲለው፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም እና የ1997 ትርጕም “መልእከተኛ” ብለውታል። በ2ኛ ነገሥት 1፥3 ውስጥ 2 ጊዜ የሚገኘው ይኸው ቃል፣ በዚያው ጥቅስ ውስጥ “መልአክ” እና “መልእክተኞች” ተብሎ ነው የተተረጐመው። በዕብራይስጡ “ማላከ ሞት” (מַלְאָךְ מָוֶת) የሚለው ስያሜ “የሞት መልእክተኛ” (ምሳሌ 16፥14)፣ “ማልአክ ሻሎውም” (מַלְאָךְ שָׁלֹום) ደግሞ “የሰላም መልእክተኞች” (ኢሳ. 33፥7) ተብሏል።[39] ማላክ የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ውስጥ 213 ጊዜ ሲገኝ፣ ለምሳሌ NIV መጽሐፍ ቅዱስ፣ 108 ጊዜ መልአክ/መላእክት፣ 83 ጊዜ መልእክተኛ/መልእክተኞች፣ 8 ጊዜ ደግሞ ልዑክ/ልዑካን (envoy, delegation, official) በማለት ተርጕሞታል።[40]

ስለዚህ ይህ “የቤቴል አምላክ”፣ “የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ” የሆነውና “ያሕዌ ነኝ” ያለው “መልአክ” በእርግጥም ያህዌ መሆኑ እንደማያጠራጥር ሁሉ፣ መልእክተኛ (የተላከ) መሆኑም አያጠራጥርም። ይህ ደግሞ አስቀድመን ካነሣነው ሐሳብ ጋር ይገጥማል። እግዚአብሔር ወልድ፣ የእግዚአብሔር አብ ልጅ የሆነው ከዘላለምም ነውና በብሉይ ኪዳን የአባቱ መልእከተኛ በመሆን (እየተላከ) ይመጣ እንደ ነበር መናገር ይቻላል። እርሱ ያሕዌም፣ የያሕዌ መልእክተኛም ነው። አብ በአባትነቱ ወልድን ይልካል፤ ወልድም በልጅነቱ ለአብ ይላካል! የእግዚአብሔር መልአክ የተሰኘው፣ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት (ቅድመ ትስጉት) የተገለጠበት መገለጫ ማንነቱ ነበር። ከሙሴ በፊት፣ ለአብርሃምም፣ ለአጋርም፣ ለያዕቆብም የተገለጠው ያ እግዚአብሔር ወልድ ነው።