Tuesday, June 9, 2015

ኢየሱስ አሁን ጠበቃ ነው ወይስ ዳኛ? 1ዮሐ. 2፥1-2 ስለ ማን ይናገራል?

ኢየሱስ አሁን ጠበቃ ነው ወይስ ዳኛ?
ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለመድረስ ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጀመር የግድ ነው፡፡ "ትንሽ ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ መጠጋት" እንደሚባለው ብሂል፥ የራስን አመለካከት ወይም ሌላ ምድራዊ ተመክሮን ይዞ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መጠጋት፥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመቀበል ሳይሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ለራስ ሐሳብ ደጋፊ አድርጎ ለማቅረብ ያለመ አካሄድ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ኢየሱስ መካከለኛነት በብዙ ስፍራ የተጻፈውን እውነት እንዳለ ለመቀበል የሚቸገሩ ሰዎች አሉ፡፡ የሚቸገሩበት ዋና ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ለራሳቸው አስተምህሮ ቅድሚያ ስለሚሰጡ ነው፡፡ ቃሉን እንዳለ ከመቀበልና የእግዚአብሔርን ሐሳብ ከማገልገል ይልቅ ከራሳቸው አስተምህሮ ጋር ለማስማማት ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውን እውነት በርዘውና ከልሰው ለእነርሱ የሚስማማ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ እንግዳ አስተምህሮን ያስተዋውቃሉ፡፡ በዚህ ሥራ ማስደሰት የሚቻለው ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን ነው?
በዚህ ዘመን የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት ለማስተባበል ከሚሠነዘሩት አስተያየቶች መካከል ምድራዊውን ተመክሮ አብነት በማድረግ፥ ስለ ኢየሱስ ጠበቃነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ለማስተባበል የሚሞከርበት አቀራረብ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ጒዳይ ላይ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡት ወገኖች፥ ኢየሱስን ጠበቃ ማድረግ የእርሱን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ እርሱ ዛሬ ዳኛ እንጂ ጠበቃ ሊሆን አይችልም ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ ከሚያቀርቧቸው የመከራከሪያ ሐሳቦች መካከል አንዱ፥ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በአብ ቀኝ መቀመጡን የተመለከተ ነው፡፡ ‘በአብ ቀኝ መቀመጡ የሚያሳየው ዳኛነቱን ነው፡፡ በምድር ላይ በፍርድ ቤት ቋንቋ ዳኛ ተሠየመ ወይም ተቀመጠ ሲባል፥ ጠበቃ ደግሞ ቆመ ይባላል፡፡ ኢየሱስ በአብ ቀኝ ተቀመጠ እንጂ ቆመ ተብሎ አልተነገረለትም፡፡ እስጢፋኖስ በተወገረ ጊዜ ግን ለጥብቅና ሳይሆን፥ በአገልጋዩ መወገር ተቈጥቶ ነው የቆመው’ ይላሉ፡፡ መቆም ማለት ማማለድ ማለት ስለ ሆነ፥ የሚቆሙ መላእክትና ቅዱሳን ናቸው ሲሉም የመካከለኛነቱን ስፍራ ለእነርሱ ይሰጣሉ፡፡
1ዮሐ. 2፥1-2 ስለ ማን ይናገራል?
በቅድሚያ ኢየሱስ ጠበቃችን መሆኑን የሚናገረውን ክፍል እንመልከት፡፡ "ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፈላችኋለሁ፡፡ ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፡፡ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ" (1ዮሐ. 2፥1-2)፡፡
ይህን ጥቅስ ለማስተባበል ከቀድሞ ጀምሮ ተከፍቶ የነበረው ዋና ዘመቻ ጥቅሱ በትክክል አልተተረጐመም፤ ወይም ተዛብቶ ነው የተተረጐመው የሚል ነበር፡፡ በተለይም ጥቅሱን ከግእዙ ዐዲስ ኪዳን ወደ ዐማርኛ ለመተርጐም የሞከሩ ክፍሎች፥ ከግሪኩ የተተረጐመውን የ1953 ዓ.ም. ዕትም መጽሐፍ ቅዱስን ቃል የተዛባ ትርጒም አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡ እነርሱ በግእዙ መሠረት ሰጠን ያሉት ትርጒም ግን የግእዙን ንባብ ያልጠበቀና ለራስ አመለካከት ደጋፊ በሆነ መንገድ የቀረበ ሆኖ ይታያል፡፡
የግእዙ ንባብ፥ "ደቂቅየ ዘንተ እጽሕፍ ለክሙ ከመ ኢተአብሱ ወእመኒ ቦ ዘአበሰ ጰራቅሊጦስ ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ ውእቱ ይኅድግ ለነ ኃጣውኢነ ወአኮ በእንቲኣነ ባሕቲቱ አላ በእንተ ዓለምኒ፡፡" ለዚህ ንባብ የተሰጠው ትርጒም እንዲህ የሚል ነው፤ "ልጆቼ ሆይ እንዳትበድሉ ይህን እጽፈላችኋለሁ፤ የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ኀጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ጻድቅ ነው፡፡ ስለ እኛ ብቻ አይደለም፤ ስለ ዓለምም ሁሉ እንጂ" (1ዮሐ. 2፥1-2 የ2 ሺህ ዓ.ም. ዕትም)፡፡ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ደግሞ "ግሪኩ ‘ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፤ እርሱም ጻድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው’" ይላል፡፡
በዚህ ትርጒም ላይ ሁለት ዐይነት ስሕተቶች ተፈጽመዋል፡፡ የመጀመሪያው የግእዙን የንባብ ሐሳብና የቃላቱን ሰዋስዋዊ አገባብ ጠብቆ አለመተርጐም ወይም ሌላ ትርጒም መስጠት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውን ቃል ሳይተረጒሙ በማለፍና እንዳለ በማስቀመጥ አንባቢው ክፍሉ ስለ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተነገረ ቈጥሮ እንዲቀበለው ማድረግ ነው፡፡
የቃላቱን ሰዋስዋዊ አገባብ በተመለከተ የተፈጸመውን ስሕተት እንመልከት፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውም መቀጸል የነበረበት ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተርጓሚዎቹ ግን ለእርሱ በመቀጸል ፈንታ ስለ ጰራቅሊጦስ (መንፈስ ቅዱስ) እንደ ተነገረ አድርገው ነው ያቀረቡት፡፡ ይህም ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን የሚለው ስለ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተነገረና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ተደርጎ እንዲታሰብ ሆኗል፡፡ የግእዙ ንባብ "ወኢየሱስ ክርስቶስ" ሳይልም ተርጓሚዎቹ "ኢየሱስ ክርስቶስም" በማለት የ"ወ" ትርጒም ሊሆን የሚችለውን "ም"ን አክለውበታል፡፡ ይህም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የሚናገረውን ዐረፍተ ነገር ከሁለት ከፍሎ ስለ ጰራቅሊጦስም እንደ ተነገረ አድርጎ ለማቅረብ ተፈልጎ ነው፡፡ እንዲህ የሆነውም በዋናነት "ጠበቃ" የሚለውን ቃል ደብዛውን ለማጥፋት እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡
"ጰራቅሊጦስ" የሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን፥ የሚከተሉት ትርጒሞች አሉት፡፡ በኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ላይ (1948፣ 907) በመጀመሪያ ትርጒሙ፥ "አማላጅ፣ አስታራቂ፣ አፍ፣ ጠበቃ፣ ትርጁማን፣ አምጃር፣ እያጣፈጠ የሚናገር፣ ስብቅል ካፉ ማር ጠብ የሚል" ማለት ነው፡፡ በሁለተኛ ፍቺው ደግሞ፥ "ናዛዚ መጽንኢ፤ መስተፍሥሒ፤ መንፈስ ቅዱስ፡፡ በዓለ ኀምሳ፤ የትንሣኤ ዐምሳኛ፣ የዕርገት ዐሥረኛ፤ እሑድ ቀን የሚውል" የሚል ትርጒም ይሰጣል፡፡ ሊቁ፥ "ወእመኒ ቦ ዘአበሰ ጰራቅሊጦስ ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ" የሚለውን ጥቅስ አስረጂ አድርገው ያቀረቡት፥ "አማላጅ፣ አስታራቂ፣ አፍ፣ ጠበቃ፣ …" በሚለው በመጀመሪያው ትርጒም ሥር ነው፡፡ ይህም "ጰራቅሊጦስ" የሚለው ቃል በ1ዮሐ. 2፥1-2 ውስጥ የተጠቀሰው መንፈስ ቅዱስን ለማመልከት ሳይሆን የኢየሱስን መካከለኛነት ለማሳየት እንደ ሆነ ያስረዳል፡፡
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ለግእዙ ንባብ በተሰጠው ትርጒም ላይ የተፈጸመው ሁለተኛው ስሕተት፥ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውን የግሪክ ቃል ሳይተረጒሙ እንዳለ የማስቀመጡ ጒዳይ ነው፡፡ በቅድሚያ እንዲህ ማድረግ ግን ለምን አስፈለገ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የግእዙ ዐዲስ ኪዳን በዚህ ጥቅስ ውስጥ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውን ቃል ወደ ግእዝ ሳይተረጒመው እንዳለ ነው ያስቀመጠው፡፡ ቃሉ በዐማርኛ ውስጥ አቻ ስላለው የ1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ "ጠበቃ" ብሎ ተርጒሞታል፡፡ የ2 ሺሁ ዓ.ም. ዕትምም በተመሳሳይ ሁኔታ ሳይተረጒመው እንዳለ "ጰራቅሊጦስ" ብሎ ነው ያስቀመጠው፡፡ በግርጌ ማስታወሻው ላይም እንዲሁ አልተረጐመውም፡፡ ለምን?
ግእዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ አምልኮ የሚፈጸምበት ዋና ቋንቋ መሆኑ ቢታወቅም፥ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፥ በተለይም ለዐማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ እድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት ባይሆንም፥ አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን ለመሰወርም አንዳንዶች ሲገለገሉበት ይታያል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ "ጰራቅሊጦስ" የሚለውን የግሪክ ቃል ሳይተረጒሙ እንዳለ ማስቀመጥ የተፈለገው አቻ ቃል ስለ ጠፋለት አይደለም፡፡ ወይም "ጰራቅሊጦስ" የሚለው ቃል ለዐማርኛ አንባብያን ሐሳቡን ይበልጥ የሚገልጥ ሆኖ ስለ ተገኘም አይደለም፡፡ ነገር ግን "ጠበቃ" ተብሎ ቢተረጐም፥ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ ለፍጡራን የተሰጠውን የመካከለኛነት ስፍራ ለባለቤቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ ተመላሽ የሚያደርግ በመሆኑ፥ ምስጢሩን ለመሰወር ነው ከማለት በቀር ሌላ ፍቺ አይሰጠውም፡፡
እንዲህ ማድረግ ዐዲስ ነገር አለመሆኑን በሌላ ማስረጃ እናስረዳ፡፡ ሃይማኖተ አበው በተሰኘው መጽሐፍ ላይ በግእዙ ንባብ ውስጥ "ሊቀ ካህናት" የሚለው ማዕርግ ለኢየሱስ ክርስቶስ በተቀጸለባቸው ክፍሎች፥ በዐማርኛው ንባብ ላይ "አስታራቂ" ተብሎ ተተርጒሟል፡፡ ለምሳሌ፦ በገጽ 222 ቊጥር 14 ላይ ያለውን መመልከት ይቻላል፡፡ እንዲህ ይላል፤ "መኑ ውእቱ ሊቀ ካህናት ምእመን ዘእንበሌሁ፤ - ከእርሱ በቀር ኀጢአትን ማስተስረይ የሚቻለው የታመነ አስታራቂ ማነው?" በዚሁ ገጽ ቊጥር 15 ላይ ግን ግእዙ "… ወኢያንሥኣ ለነ ሊቀ ካህናት እመላእክት ወኢእምኀይላት እለ እሙንቱ ይቀውሙ ዐውደ መንበሩ" የሚለውን ግን በዐማርኛው ላይ ሳይተረጒሙት "… ዙፋኑን ከበው ከሚቆሙ ከመላእክት ከኀይላትም ወገን ሊቀ ካህናት አልሾመልንም" ብለው እንዳለ ነው ያስቀመጡት፡፡ ለምን ሳይተረጒሙት ቀሩ? ቢባል፥ "መላእክትን አስታራቂ አድርጎ አልሾመልንም" እንዳይልባቸው ነው እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ ስለዚህ እውነቱን በግእዝ ሸፈኑት ማለት ነው፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ግእዝ እውነትን ለመሰወር አላገለገለምን? እንዴታ!!
እስካሁን የተመለከትናቸው ማስረጃዎች፥ 1ዮሐ. 2፥1-2 የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ጠበቃነት እንጂ ጰራቅሊጦስ ስለ ተባለው ስለ መንፈስ ቅዱስ እንዳልሆነ ያስረዳሉ ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ በላይ ግን የጥቅሱን ዐውዳዊ ፍቺ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ የሐዋርያው ዮሐንስ መልእክት ምዕራፍ 2 የሚጀምረው፥ "ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፈላችኋለሁ፤ ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፡፡ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ" በማለት ነው፡፡
ዮሐንስ በዚህ ክፍል ክርስቲያኖች ኀጢአትን ማድረግ እንደሌለባቸው ይናገራል፡፡ ምክንያቱም በዚሁ መልእክት (3፥4-10) ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ የእርሱ ዘር በውስጡ ስላለ ኀጢአትን ሊያደርግ አይችልም፡፡ ደግሞም በክርስቶስ የማዳን ሥራ አምኜ በእርሱ እኖራለሁ የሚል ማንም ቢኖር ኀጢአትን አያደርግም፡፡ በእርሱ እኖራለሁ እያለ ኀጢአትን የሚያደርግ እርሱ ግን ራሱን በከንቱ እየሸነገለ ነው እንጂ ጌታን አላየውም፤ አላወቀውምም፡፡ ለምን ቢባል በጌታ ዘንድ ኀጢአት የለም፡፡ እርሱ በሥጋ የተገለጠውም ኀጢአትን ለማስወገድ ነው እንጂ በኀጢአት እንድንኖር አይደለም፡፡ እንዲያውም የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች የሚለዩት፥ ጽድቅን በማድረግና ባለማድረግ፥ ወይም ኀጢአትን በመሥራትና ባለ መሥራት ነው፡፡
ይህ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባው የጽድቅ ሕይወት ልኩ የት ድረስ እንደ ሆነ ያሳያል፡፡ "ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ" ሲል በማስጠንቀቅ የጀመረውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ክርስቲያኖች እንዲህ ሊኖሩ የተጠሩ ቅዱሳን ቢሆኑም፥ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ካመኑበት ቅጽበት ጀምሮ ኀጢአተኛው ባሕርይ ከውስጣቸው በእምነት ተገድሏል እንጂ ከውስጣቸው ተመጥጦ ገና አልተወገደና ኀጢአትን ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይኸው ሐዋርያ "ኀጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም" (1ዮሐ.1፥8) ያለውም ስለዚህ ነው፡፡
ክርስቲያኖች ኀጢአት ሠርተው ቢገኙስ? ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነው? በፍጹም!! ተስፋ አላቸው እንጂ፡፡ ምክንያቱም፥ "ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፡፡ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ" ተብሏል፡፡ ከዚህ የምንገነዘበው፥ ኀጢአትን አድርገን ብንገኝ በአብ ዘንድ የሚገኝ የኀጢአታችን ማስተስረያ የሆነው ጠበቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላለን እርሱ ነጻ እንደሚያደርገን ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ አንድ ጊዜ ያቀረበው መሥዋዕት ለተወሰነ ጊዜ የሚያገለግልና የተወሰኑ ወይም ጥቂቶች ኀጢአቶችን ብቻ የሚያስተሰርይ አይደለም፤ አንድ ጊዜ የቀረበ ፍጹም፣ ሕያውና ዘላለማዊ መሥዋዕት በመሆኑ የክርስቲያኖችን ብቻ ሳይሆን፥ በክርስቶስ የማዳን ሥራ አምነው፥ አሁንና ወደ ፊት የሚመጡትን ሰዎች ኀጢአት ሁሉ ለማስተስረይ በቂና ችሎታ ያለው መሥዋዕት ነው፡፡ ስለዚህ መበደል የለብንም እንጂ ብንበድል በዚሁ መሥዋዕት እንታረቃለን ማለት ነው፡፡
የኢየሱስ ጠበቃነት በምድራዊ ጥብቅና ይመዘናልን?
በመነሻችን ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጀመር ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ያደርሳል ብለናል፡፡ ሌላ ምድራዊ ተመክሮን መነሻ አድርገን መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መሞከር ግን፥ ይዘን ወደ ተነሣነውና ወደምንፈልገው ነገር እንጂ እግዚአብሔር በቃሉ ወደ ገለጠው እውነት አንደርስም፡፡ ኢየሱስ ጠበቃ መሆኑን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚቃወሙ ሰዎች ችግርም ይኸው ሆኖ ይታያል፡፡
ኢየሱስ ፈራጅ እንጂ ጠበቃ ሊሆን አይችልም የሚለውን አመለካከት የሚያቀነቅኑት ክፍሎች ጥቅሱን ለመቃወም መነሻ የሚያደርጉት ምድራዊውን ተመክሮ ነው፡፡ "ጠበቃ፥ ባለጒዳይን ወክሎ በፍርድ ቤት የሚከራከር፣ የሚሟገት፣ ነገረ ፈጅ" መሆኑ ይታወቃል (የዐማርኛ መዝገበ ቃላት 1993፣ 546)፡፡ ጠበቃ፥ የወከለውን ባለጒዳይ ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ወይም ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሕግ አናቅጽን ጠቅሶ የሚከራከር ባለሙያ ነው፡፡ ሲከራከርም ደንበኛዬ ጥፋት የለበትም ወይም ጥቅሙ ተነክቷል የሚልና በተቃራኒው የቆመውን ወገን ጥፋተኛ የሚያደርግ መሠረት ይዞ ነው፡፡ አንዳንዱ ጠበቃ ደንበኛው ጥፋተኛ ቢሆንም እንኳ ሊረታ የሚችልበት ዕድል ካለው ጥፋተኛ አይደለም ሲል ሊከራከር ይችል ይሆናል፡፡ ትክክለኛ ያለሆነውን ጒዳይ በሚያቀርባቸው መከራከሪያዎችና በሚጠቅሳቸው የሕግ አናቅጽ በችሎት ፊት ቀርቦ ማስረዳት፣ ማሳመንና መርታት ከቻለም ደንበኛውን ነጻ ሊያደርግ፥ ጥቅሙንም ሊያስጠብቅለት ይችላል፡፡
"ኢየሱስ ጠበቃ ነው" የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት፥ ከዚህ ምድራዊ የጥብቅና ሙያ ጋር ካነጻጸርነው በርግጥም ለመቀበል ያስቸግራል፡፡ የኢየሱስን ጠበቃነት ለመረዳት መነሣት ያለብን ከምድራዊ የጥብቅና ተመክሮ ሳይሆን ቃሉን ከተናገረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ጠበቃ ነው ሲል እንደ ምድራዊ ጠበቃ በአብ ፊት ቆሞ እያንዳንዱን ኀጢአተኛ (ያለማንነቱ) ንጹሕ ነው እያለ ይከራከርለታል፤ ያስምረዋል፤ ከተጠያቂነትም ነጻ ያደርገዋል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ስለ ኀጢአተኞች አንድ ጊዜ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት በእርሱ በኩል አምነው የሚቀርቡት ሁሉ በየዕለቱ ይታረቁበታል፤ ስርየትን ያገኙበታል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው በምዕራፍ 1፥7 ላይ፥ "የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል" ብሏል፡፡ በተጨማሪም፥ "እርሱም (ኢየሱስ ክርስቶስ) የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፡፡ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ" በማለት፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ለኀጢአት ሁሉ በቂ የሆነ መሥዋዕት መሆኑን አስረድቷል፡፡ ይህም የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት የሚያመለክት ነው፡፡
ሌላው ከምድራዊ ተመክሮ ጋር የተያያዘው የእነዚሁ ወገኖች የመከራከሪያ ነጥብ፥ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ፥ ጠበቃ ሳይሆን ፈራጅ (ዳኛ) እንደ ሆነ ተጽፏልና፥ እርሱ በአንድ ጊዜ ጠበቃም ዳኛም እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚል ነው፡፡ በመሠረቱ አሁንም ይህ ምድራዊ ተመክሮን መነሻ ያደረገ የእነርሱው አመለካከት እንጂ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ነገሩን በዚህ መልክ አላቀረበልንም፡፡ ለዚህ መከራከሪያ በጮራ ቊጥር 39 በገጽ 6 ላይ "ኢየሱስ አሁን ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም" በሚለው ነጥብ ሥር ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ በዚያ መሠረት፥ ኢየሱስ ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ለኀጢአተኛውና በእርሱ የማዳን ሥራ አምኖ ለሚመጣ ሁሉ፥ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት መካከለኛው ወይም አዳኙ ነው እንጂ በማንም ላይ አይፈርድም፡፡ የማያምን ቢኖርና ባለማመኑ ቢጸና ግን ከአሁን ጀምሮ ባላመነበት ጊዜ ሁሉ ከፍርድ በታች ነው (ዮሐ. 3፥18)፡፡ ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ ሲመጣ ደግሞ ፈራጅ ሆኖ ነው የሚገለጠው፡፡ ስለ ሆነም በዚህ መንገድ ኢየሱስ ጠበቃ ነው ቢባል፥ የመካከለኛነቱን ግብር በትክክል ይገልጻል እንጂ የእርሱን ክብር ዝቅ የሚያደርግበት አንድም ምክንያት የለም፡፡
ኢየሱስ በአብ ቀኝ መቀመጡ መካከለኛነቱን አስቀርቶታልን?
ብዙዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሳለ እስከ ተሰቀለበት ጊዜ ድረስ መጸለዩንና መማለዱን በአጠቃላይም የመካከለኛነት ሥራውን መፈጸሙን አይክዱም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በግልጽ ያስረዳልና (ኢሳ. 53፥12፤ ማቴ. 11፥25፤ 14፥23፤ 26፥36-44፤ ማር. 1፥35፤ 6፥46፤ ሉቃ. 22፥31-32፤ 23፥34፤ ዮሐ. 17፥9-26፤ ዕብ 5፥7-10)፡፡ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ የእነዚህን ጥቅሶች ግልጽ መልእክት በትርጒሜ እያጠየሙ ደብዛዛ ያደርጉታል፡፡ ጌታችን በፈቃዱ ያደረገውንና ያላፈረበትን፥ ነቢያትና ሐዋርያትም ተቀብለው ሳይቀላቅሉና ሳይሸቃቅጡ ለእኛ ያስተላለፉትን የመካከለኛነቱን ሥራ ለማመን የምንቸገረው ከቶ ለምን ይሆን?
ጌታ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ በክብር ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፡፡ በዚያ የተቀመጠው በክብር እንጂ በዚህ ምድር እንደ ነበረው ዝቅ ብሎ አይደለም፡፡ ቢሆንም ዛሬም ፍጹም አምላክ፥ ፍጹም ሰው ነው፡፡ በዚያ የሚገኘውም አንድ ጊዜ በፈጸመው የማዳን ሥራው አምነው በእርሱ በኩል ለሚመጡት የመዳናቸው ምክንያት ሆኖ ነው፡፡ ይህን ሲያስረዳ የዕብራውያኑ ጸሓፊ እንዲህ ብሏል፤ "እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት … ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው" (ዕብ. 5፥7-10)፡፡
ዛሬ ሰዎች በስሙ ወይም በእርሱ በኩል ሲጸልዩ፥ እርሱ በአብ ፊት ስለ እነርሱ አይጸልይ አይማልድ እንጂ፥ በቀደመው ልመናውና ምልጃው ምሕረትን እንዲቀበሉ ምክንያቱ እርሱው ብቻ ነው፡፡ ጌታ በሊቀ ካህናትነቱ አንድ ጊዜ ያቀረበው ልመና ለዘላለም የሚያገለግልና በስሙ አምነው በእርሱ በኩል የሚመጡትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ሕያው ልመና ነውና፡፡ ጌታ ሲጸልይ፥ የሚለምነው በጊዜው በአጠገቡ ስለ ነበሩት ስለ ደቀ መዛሙርቱ ብቻ እንዳልሆነና የእነርሱን ስብከት ሰምተው በክርስቶስ አዳኝነት ስለሚያምኑና እስከ ኅልፈተ ዓለም ስለሚነሡ ምእመናን ጭምር እንደ ሆነ ገልጧል (ዮሐ. 17፥20-21)፡፡ ኢየሱስ ዛሬም መካከለኛ ነው ሲባል አንድ ጊዜ ያቀረበው ይህ ጸሎቱና መሥዋዕቱ ለሁል ጊዜም ያገለግላል ማለት ነው እንጂ እርሱ በክብር ከሚገኝበት የአብ ቀኝ፥ በዚህ ምድር ወደ ነበረበት ሁኔታው ዝቅ ይላል ማለት እንዳይደለ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡
እውነቱ ይህ ነው፡፡ ብዙዎቹ ስለ ኢየሱስ መካከለኛነት የሚናገሩት ጥቅሶች ኢየሱስን መካከለኛ ነው የሚሉት እስከ መስቀል ሞት ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ኢየሱስ በክብር ወደ ሰማይ ካረገና በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ በኋላም ባለው ጊዜ ሁሉ መካከለኛ እንደ ሆነ ይናገራሉ እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር በኀላፊ አንቀጽ (Past Tense) "ነበረ" ብለው ሳይሆን፥ በአሁንና ቀጣይነትን በሚያመለክቱ አናቅጽ (Present and Future Tenses)፦
"ስለ እኛ የሚማልደው" (ሮሜ 8፥34)፣
"ስለ እነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል" (ዕብ. 7፥25)
"በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው (የነበረው አላለም) መካከለኛው አንድ ነው" (1ጢሞ. 2፥5)፣
"ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን (ነበረን አላለም)" (1ዮሐ. 2፥1-2) እያሉ ነው የሚናገሩት፡፡
በተለይም በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ተደጋግሞ እንደ ተገለጸው፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ያረገው፣ በእጅ ወዳልተሠራችውና በእግዚአብሔር ወደ ተተከለችው መቅደስ የገባውም አንድ ጊዜ ባቀረባቸው ምልጃና መሥዋዕት ስለ እኛ ሊቀ ካህናት ሆኖ በእውነተኛዪቱ መቅደስ ለማገልገል ነው (ዕብ. 6፥17-20፤ 7፥27-28፤ 8፥1-2፤ 9፥10-11፡24 10፥12-14፡19-20)፡፡ ያንቀላፉና በሕይወተ ሥጋ ያሉ ቅዱሳን ወደ እግዚአብሔር የቀረቡትና የሚቀርቡት፥ በአንድ አካል የተያያዙትም በእርሱ መካከለኛነት በኩል ነው፡፡ ስለዚህ በአብ ቀኝ መቀመጡ በክብሩ ሆኖ የሚያከናውነውን የመካከለኛነቱን ሥራ አላስቀረውም፡፡ ይህ አገልግሎት የእርሱው ብቻ እንጂ ላንቀላፉ ቅዱሳን ተላልፎ የተሰጠ አይደለም፤ አሁን ባለበት ሁኔታም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ተብሏልና (1ጢሞ. 2፥5፤ ዕብ. 9፥15፤ 12፥24)፡፡
ቅዱሳን መካከለኞች አይደሉምን?
"ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኀይል ታደርጋለች" (ያዕ. 5፥16) በተባለው መሠረት፥ ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ ስለ ሌሎች ይጸልዩ ነበር፡፡ ካንቀላፉ በኋላ ግን ስለዚህ ጒዳይ በግልጽ የተጻፈ ነገር የለም፤ ቢያንቀላፉም ሕያዋን ናቸውና ሊጸልዩ ይችላሉ ቢባል እንኳ፥ በምድር ላይ ከሚገኙ ሕያዋን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌላቸው ሕያዋኑ ለእነርሱ የ"ጸልዩልኝ" ርእሰ ጸሎት መስጠት አይችሉም፡፡ ለክርስቶስ ጥላና ምሳሌ ስለ ነበሩት የብሉይ ኪዳን መካከለኞች የተጻፈውም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡
የእነርሱ አገልግሎት በሞት የተገደበና ካንቀላፉ በኋላ የማይቀጥል ነበር፡፡ መካከለኞቹ ብዙዎች የሆኑበት ዋናው ምክንያትም አንዱ ሲሞት በሌላው ይተካ ስለ ነበረ ነው፡፡ "እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው" (ዕብ . 7፥23) የሚለውም ቃል ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳን ምንም እንኳ መካከለኞች ተብለው ባይጠሩም፥ ስለ ሌሎች በሚጸልዩት ጸሎትና በሚያቀርቡት ምልጃ ከዚህ የተለየ ማንነት እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡ ጸሎትና ምልጃቸውም ቅድመ እግዚአብሔር የሚያርገው የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ፥ "እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል" (ዮሐ. 16፥23) በማለት በእርሱ በኩል እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የክርስቶስን የመካከለኛነት ስፍራ ለቅዱሳን ለመስጠት የሚፈልጉ ክፍሎች፥ ይህን ሐሳባቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አድርገው ለማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ረገድ ማስረጃ ይሆነናል ብለው ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች መካከል አንዱ፥ "… እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን" (2ቆሮ. 5፥20) የሚለው ጥቅስ ነው፡፡ ይህ ጥቅስ ስላንቀላፉ ቅዱሳን አማላጅነት ይናገራል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ እንደ ማስረጃ የተወሰደው ጥቅሱ ይህን ሐሳብ ስለሚደግፍ አይደለም፤ ነገር ግን "እንደሚማልድ" በሚለው ቃል ውስጥ፥ "ል" ከሌሎቹ ፊደላት ደመቅ ብላ ስለ ተጻፈች፥ በመጀመሪያ "ለ" የነበረውን ደልዘው "ል" አድርገዉት ነው በሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ "ለ" ቢሆን ኖሮ ጥቅሱ "… እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ …" የሚል ፍቺ ይሰጥ ነበር፡፡ ይህም እግዚአብሔር በቅዱሳን እንደሚለመን ያሳያል፡፡ "ለ" ወደ "ል" ስትለወጥ ግን የቅዱሳንን ማማለድ ያስቀራል የሚል ነው ክርክሩ፡፡
በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ ባያከራክርም፥ ከጽሑፍ ሥራው አንጻር በዝግጅትና በኅትመት ሂደት ውስጥ ጥቃቅን የፊደል ስሕተት ማጋጠሙ አይቀርም፡፡ አንዳንዱ ስሕተት በዐረፍተ ነገሩ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ለውጥ የማያመጣ ሲሆን፥ አንዳንዱ ግን የትርጒም ለውጥ ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ፥ በ1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢዮ. 33፥14 ላይ "እግዚአብሔር" ማለት የነበረበትን "አግዚአብሔር" ይላል፡፡ ይህ የፊደል ስሕተት ነው፤ መታረም አለበት፡፡ ሆኖም ስሕተቱ የትርጒም ለውጥ አያስከትልም፡፡ "… እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ …" የሚለው የ2ቆሮ. 5፥20 የፊድል ስሕተት ግን የትርጒም ለውጥ እንደሚያስከትል ከዐውደ ምንባቡ መረዳት ይቻላል፡፡
"… እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ …" ቢባል ስሕተቱ ከምን ላይ ነው? ስሕተቱን ለመረዳት በቅድሚያ ዐውዱ ስለ ምን እንደሚናገር መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ከቊጥር 18 ጀምሮ ያለውን ስንመለከት፥ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ እንደ ነበረና በሐዋርያቱ ውስጥም የማስታረቅን ቃል እንዳኖረ ይናገራል፡፡ በዚሁ የማስታረቅ ቃል አማካይነት ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ የሚገባቸውን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለው እንደሚለምኗቸው በክፍሉ ውስጥ እናነባለን፡፡
እግዚአብሔር አስቀድሞ በክርስቶስ አማካይነት ዓለሙን ከራሱ ጋር እንዳስታረቀና በእርሱ የተከናወነውን ዕርቅ ያልሰሙና ያልተቀበሉ ሰዎችን ደግሞ የማስታረቁን ቃል በውስጣቸው ባስቀመጠው አገልጋዮች በኩል ዛሬም እየጠራቸው እንደ ሆነ ነው የምንረዳው፡፡ "ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን" ከሚለው አነጋገርም የምናስተውለው፥ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር መለመናቸውን ሳይሆን፥ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ወደሚፈጽሙት ዕርቅ መጋበዛቸውን ነው፡፡ የ2 ሺሁ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስም "ከእግዚአብሔር ጋር ትታረቁ ዘንድ በክርስቶስ እንለምናችኋለን" ነው የሚለው፡፡ የክፍሉ መልእክት ይህ ሲሆን፥ "እንደሚማልድ" የሚለው ቃል "እንደሚማለድ" በሚለው ቢተካ ግን ትርጒም ያጣል፤ ምክንያቱም በዚህ ክፍል የጌታ አገልጋዮች ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ስለ ማለታቸው እንጂ ጌታን ስለ መማለዳቸው አልተነገረም፡፡ ስለዚህ ይህን ስሕተት ማስተካከል የእግዚአብሔር ቃል በትክክለኛው መንገድ እንዲነበብና እንዲተረጐም ከማድረግ በቀር ሌላ የተለየ ነገር አለው ብሎ ማሰቡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ "ለ" ወደ "ል" መለወጡ ትክክለኛ ዕርማት ነው እንጂ የቅዱሳንን ምልጃ ከማስተባበል ጋር አንዳች ግንኙነት የለውም፡፡
ደግሞም ዕርማቱን ሊሰጥ የሚችለው መጽሐፍ ቅዱሱን ከዕብራይስጥና ከግሪክ ወደ ዐማርኛ ያስተረጐመው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በመሆኑ፥ የማስተካከል መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሊቀርብ የሚገባው ጥያቄ ለምን ተስተካከለ ሳይሆን፥ የተስተካከለው የግሪኩ ዐዲስ ኪዳን የሚለውን መሠረት አድርጎ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት? የሚል መሆን ይገባዋል፡፡

Written by Chorra megazine

Tuesday, March 31, 2015

ኢየሱስ የተሰቀለው ሮብ ነው ወይስ አርብ??

ማቴ 12: 40 ያለውን በመጥቀስ ነው "ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።"

ኢየሱስ ክርስቶስ "የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።" ስላለ: ይህ እንዲሙዋላ በግድ "ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት" በመቃብር ማሳለፍ አለበት::

ስለዚህ ኢየሱስ የተሰቀለው ሮብ ነው የሚል የተሳሳተ መረዳት ላላቸው ሰዎች ዝርዝር የሆነ መልስ

1. መጀመርያ በአይሁዳውያን ባህል ወይም በመፅሐፍ ቅዱስ ቃል ያለው ሰንበት አንድ ነው እሱም ቅዳሜ ነው እንጂ ሁለት ሰንበት የለም

ኦሪት ዘጸአት  20:8-9 "የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።"

አንዳንዶች ዘሌ 23:5-7 ጠቅሰው ሁለት ሰንበት ነበረ ይላሉ
"በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። በዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን ለእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ነው ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብሉ። በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።"

እነሱ ይህን ጥቅስ ተደግፈው "የእግዝአብሔር ፋሲካ" ይህ ቀን ሰንበት ተብሎ ይጠራል ይሉና ይህ ቀን ደግሞ ሐሙስ ስለሆነ ኢየሱስ የተሰቀለው ሮብ ነው ይላሉ:: ስለዚህ እንደነሱ ከሆነ ሮብ ግማሽ ቀን ስለሆነ አይቆጠርም: የሚቆጠረው ከሮብ ማታ ጀምሮ ነው ይሉናል:: ሁላችንም እንደምናውቀው የእራኤላውያን ሰንበት ቅዳሜ ነው:: ታዲያ ይህ ሰንበት (ቅዳሜ) የሚጀምረው ከአርብ ከምሽቱ አስራሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ከምሽቱ አስራሁለት ሰዓት ነው:: በመፅሐፍ ቅዱስም እግዝአብሔር አንድ ቀን ብሎ ሲጠራ መጀመርያ የሚጀምረው ከሌሊት ነው...
ዘፍጥረት 1
5              እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን።
8              እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን።
18           በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ እግዚአብሔርም መልካም እንደ ሆነ አየ።
19           ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።

ስለዚህ እስራኤላውያን ይህን የእግዝአብሔር ቀን አቆጣጠር ስለሚረዱ: እነሱም አንድ ሙሉ ቀን የሚጀምሩት ከማታ ጀምሮ ነው:: ስለዚህ ለምሳሌ ቅዳሜ የሚጀምረው ከአርብ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ነው ቅዳሜ ደግሞ የሚያልቀው ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ነው::

በእዚህ ትክክለኛ በሆነ የመፅሐፍ ቅዱስም ሆነ የእስራኤላውያን አቆጣጠር ከቆጠርን

ኢየሱስ የተሰቀለው ሮብ ነው የሚሉ ሰዎች እንደ እነሱ ሃሳብ ከሆነ ማታ ማታዎቹን እንቁጠራቸው....
·         ሮብ 12 ሰዓት በሁዋላ ሐሙስ ምሽት ነው --- አንድ ሌሊት
·         ሐሙስ 12 ሰዓት በሁዋላ አርብ ምሽት ነው --- ሁለተኛ ሌሊት
·         አርብ 12 ሰዓት በሁዋላ ቅዳሜ ምሽት ነው --- ሶስተኛ ሌሊት
·         ቅዳሜ 12 ሰዓት በሁዋላ እሁድ ምሽት ነው --- አራተኛ ሌሊት
እንግዲህ እንደነዚህ ሰዎች መረዳት ከሆነ: ኢየሱስ አራት ሌሊቶችን ነው በመቃብር ያሳለፈው ማለት ነው ምክንያቱም መፅሐፍ ቅዱስ ሲነግረን ኢየሱስ ከመቃብር የተነሳው እሁድ ማለዳ ነው (ማር 16:9)

ማር 16:9 "ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ። When Jesus rose early on the first day of the week"

ኢየሱስ የተሰቀለው ሮብ ነው የሚሉ ሰዎች: እንደ እነሱ ሃሳብ ቀኖቹን እንቁጠራቸው....
ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው 6 ሰዓት ላይ ሲሆን የሞተው ደግሞ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነው:: ስለዚህ
·         ሮብ ቀን --- ግማሽ ቀን
·         ሐሙስ ቀን --- አንድ ሙሉ ቀን
·         አርብ ቀን --- አንድ ሙሉ ቀን
·         ቅዳሜ ቀን --- አንድ ሙሉ ቀን
እንግዲህ እንደነዚህ ሰዎች መረዳት ከሆነ: ኢየሱስ ሶስት ሙሉ ከግማሽ ቀን ነው በመቃብር ያሳለፈው ማለት ነው::

በእዚያ ላይ ከላይ እንዳየነው እንደነዚህ ሰዎች መረዳት ከሆነ ኢየሱስ ተሰቅሎ ከሞተ ሶስተኛው ቀን ቅዳሜ (ሰንበት) ነው:: መፅሐፍ ቅዱስ ግን ኢየሱስ ተሰቅሎ ከሞተ ሶስተኛው ቀን ቅዳሜ (ሰንበት) ካለፈ በሁዋላ በሳምንቱ የመጀመርያ ቀን እሁድ እንደሆነ ነው የሚነግረን::

ሉቃስ 24
1 ነገር ግን #ከሳምንቱ_በመጀመሪያው_ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም።.....  13 እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ #በዚያ_ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ 14 ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። 15 ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ 16 ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር። 17 እርሱም። እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው። 18 ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ። አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው። 19 እርሱም። ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤ 20 እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። 21 እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር #ይህ_ከሆነ_ዛሬ_ሦስተኛው_ቀን_ነው።... 45 በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ 46 እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል #በሦስተኛውም_ቀን ከሙታን ይነሣል፥."

እዚህ ጋር በጣም በግልፅ እንደምናየው: እነእዚህ የኤማዎስ መንገደኞች ለኢየሱስ ለእራሱ እሱ መሆኑን ሳያውቁ: ኢየሱስ በመሰቀል ላይ ከተሰቀለ ይህን ለእሱ በሚነግሩበት ቀን ላይ "ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው" ብለው እየነገሩት ነው:: "ዛሬ" የሚሉት ደግሞ ቁጥር 1 ላይ እንደምናየው "በሳምንቱ በመጀመርያው ቀን" ነው:: ቀን ደግሞ እሁድ ነው:: ኢየሱስ ሲያስረዳቸው በመጨረሻ "በሦስተኛው ቀን" ከሙታን ይነሳል ነው ያላቸው::

ስለዚህ ሮብ ተሰቀለ ለሚሉ ሰዎች በእነሱ መረዳት መሠረት ሶስተኛው ቀን ቅዳሜ ሲሆን መፅሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉ ሰዎች ደግሞ ሶስተኛው ቀን እሁድ ነው::

ሌላው የእነዚህ ሮብ ተሰቀለ የሚሉ ሰዎች መከራከርያ ነጥብ: ኢየሱስ በማቴ 12: 40 ያለውን በመጥቀስ ነው "ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።"

ኢየሱስ ክርስቶስ "የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።" ስላለ: ይህ እንዲሙዋላ በግድ "ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት" በመቃብር ማሳለፍ አለበት ይላሉ::

መጀመርያ ኢየሱስም ሆነ ሌሎች ስለዚህ ምን እንዳሉ እናስቀምጥ በተለያየ ቦታ...

#በሦስተኛውም_ቀን (On the third day)
ማቴ 17:22-23 "በገሊላም ሲመላለሱ ኢየሱስ። የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፥ ይገድሉትማል፥ #በሦስተኛውም_ቀን ይነሣል አላቸው። እጅግም አዘኑ።
ማቴ 20:19 " ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ #በሦስተኛውም_ቀን ይነሣል አላቸው።"
ሉቃ 19:21-22 "እርሱ ግን። የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊጣል ሊገደልም #በሦስተኛውም_ቀን ሊነሣ ይገባዋል ብሎ ለማንም ይህን እንዳይናገሩ አስጠንቅቆ አዘዘ።"
የሐዋ ሥራ 10:40 "እርሱን እግዚአብሔር #በሦስተኛው_ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤
1 ቆሮ 15:4  " መጽሐፍም እንደሚል #በሦስተኛው_ቀን ተነሣ፥"

 #ከሦስት_ቀን_በኋላ  After three days
ማቴ 27 63 "ጌታ ሆይ፥ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። #ከሦስት_ቀን_በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን።"
ማር 8:31 የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም #ከሦስት_ቀንም_በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር።

እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን የተነሳው መቼ ነው ለሚለው መፅሐፍ ቅዱስ እነዚህ መልሶች አሉት....
·         ከሶስት ቀንና ከሶስት ሌሊት በሁዋላ
·         በሦስተኛውም ቀን
·         በሦስተኛው ቀን
·         ከሦስት ቀን በሁዋላ

እንግዲህ ኢየሱስ በመቃብር የቆየውሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት” የሚለውን ወስደን “72 ሰዓት” ካደረግነው: በእዚህ መረዳት ከቃሉ ጋር ልንጋጭ ነው:: ምክንያቱም 72 ሰዓት በሁዋላ ከተነሳ: ከሦስት ቀን በሁዋላ የሚለው ጥቅስ እንጂ: በሦስተኛውም ቀን ሆነ: በሦስተኛው ቀን: የሚሉት ጥቅሶች ጋር ልንጋጭ ነው:: ቃሉ ደግሞ አይጋጭም:: ስለዚህ "ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት" የሚለው ነገር "ሶስት ቀን" ወይም "በሶስተኛው ቀን" ለማለት በጊዜው የሚጠቀሙበት አባባል እንጂ 72 ሰዓት ማለት አይደለም:: ለምሳሌ መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ "ሰውን" ለመጥቀስ "ሥጋና ደም" የሚል አባባል አለ:: ልክ እንደዛ "ሶስት ቀን" ለማለት የሚጠቀሙበት አባባል ነው::

ሌላ ምሳሌ ከመፅሐፍ ቅዱስ
የማቴዎስ ወንጌል ኢየሱስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደፆመ ይነግረናል
ማርቆስና ሉቃስ ደግሞ አርባ ቀን እንደፆመ ይነግሩናል

ስለዚህ አርባ ቀንና ሌሊት ማለት አርባ ቀን ማለት ነው

ሌላ ምሳሌ ከመፅሐፍ ቅዱስ...
"ከሶስት ቀንና ከሶስት ሌሊት በሁዋላ" የሚለው አባባል 72 ሰዓት ነው የሚል መረዳት ላላቸው --- መፅሐፍ ቅዱስ ይህን "አራተኛው ቀን" ነው የሚለው
የሐዋ ሥራ 10 ...
1 በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።
ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል። ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። ---- የመጀመርያ ቀን
9 እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ። --- ሁለተኛ ቀን
23 እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፥ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። --- ሦስተኛ ቀን
24 በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር።  --- አራተኛ ቀን
30 ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው። #በዚች_ሰዓት_የዛሬ_አራት_ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና።"

ከእዚህ እንደምንረዳው ልክ መልዐኩ በመጣበት ቀንና: ሰዎቹ ተልከው ጴጥሮስ ጋር ሲደርሱ -- 24 ሰዓት
ጴጥሮስ ከእነሱ ጋር ተነስቶ ሲሄድ --- 24 ሰዓት
በነጋታው ጴጥሮስ ከቆርኔሊዎስ ጋር ተገናኝቶ ቆርኔሊዎስ ስለሁኔታው ሲነግረው --- 24 ሰዓት
በጠቅላላው 72 ሰዓቶች በሰዎቹ ቀን አቆጣጠር ግን 4 ቀኖች

ሌላ ምሳሌ ከመፅሐፍ ቅዱስ...
ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት የሚለው አባባል ሶስት ቀን ለማለት እንጂ 72 ሰዓት ማለት እንዳልሆነ
1 ሳሙ 30 12- 13 "ከበለሱም ጥፍጥፍ ቁራጭና ሁለት የወይን ዘለላ ሰጡት #ሦስት_ቀንና_ሦስት_ሌሊት እንጀራ አልበላም ውኃም አልጠጣም ነበርና በበላ ጊዜ ነፍሱ ወደ እርሱ ተመለሰች። ዳዊትም፦ አንተ የማን ነህ? ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም፦ እኔ የአማሌቃዊ ባሪያ ግብጻዊ ብላቴና ነኝ #ከሦስት_ቀንም_በፊት ታምሜ ነበርና ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ።"

ሌላ ምሳሌ ከመፅሐፍ ቅዱስ
ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑንማለት ሦስት ቀን ማለት ነው እንጂ 72 ሰዓት ማለት አይደለም
አስ 4:16; እና አስ 5:1

4:16 "ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ፥ ለእኔም ጹሙ #ሦስት_ቀን_ሌሊቱንና_ቀኑን አትብሉም፥ አትጠጡም እኔና ደንገጥሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን ምንም እንኳ ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ ብጠፋም እጠፋለሁ።"

5:1 "#በሦስተኛውም_ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳ በንጉሡ ቤት ትይዩ በንጉሡ ቤት በውስጠኛው ወለል ቆመች ንጉሡም በቤቱ መግቢያ ትይዩ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በንጉሡ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ነበር።

የእስራኤላውያን ታሪክ ያጠኑ ሰዎች እንደሚሉት ሌሎቹ ቀኖች "የመጀመርያው ቀን": "ሁለተኛው": "ሶስተኛው" እያሉ ሲጠሩ አርብን ግን ስድስተኛው ቀን ብለው አይጠሩትም:: ልክ ቅዳሜን ሰባተኛው ቀን ብለው እንደማይጠሩት:: ስለዚህ አርብን
በአማርኛ - የመዘጋጃው ቀን
በእንግሊዘኛው - reparation day
በአራማይክ -  arubta
በግሪኩ - paraskeue
ብለው ነው ነው የሚጠሩት:: ኢየሱስ የተሰቀለው ደግሞ አርብ ለሰንበት የማዘጋጀት ቀን ነበር የተሰቀለው::
ስለዚህ ኢየሱስ
ለሰንበት በማዘጋጃ ቀን ተሰቀለ ከእዛም ሰንበት ካለፈ በሁዋላ ተነሳ -ማቴ 27:62; 28:1
--ማር 15:42; 16:1

ሌላው ኢየሱስ ሮብ ነው የተሰቀለው የሚሉ ሰዎች ለመከራከርያ የሚያቀርቡት ማር 16:1 ነው ...

"ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ።"

እነሱ እንደሚሉት ከሆነ ሮብ ኢየሱስ ተሰቀለ ሐሙስ ሰንበት ነበር ከእዛ አርብ ሽቶና የሚያስፈልገውን ገዙ: ከእዛም ሁለተኛው ሰንበት ካለፈ በሁዋላ እሁድ ጥዋት ወደመቃብሩ መጡ ነው::

ይህ ስህተት የመጣው የአይሁድን ቀን አቆጣጠር ካለመረዳት ነው:: ምክንያቱም ከላይ እንዳስቀመጥኩት ሰንበት የሚጀምረው በአይሁድ አቆጣጠር አርብ ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲሆን: ሰንበት የሚያልቀው ደግሞ ቅዳሜ ከምሽቱ 12 ሰዓት ነው:: ስለዚህ እነዚህ ሴቶች ቅዳሜ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚፈልጉትን መግዛት ይችላሉ ሰንበት ስላለፈ:: ይህ የአይሁድ አቆጣጠር ከገባን ወደማይሆን ስህተት አንገባም::

ሌላው ኢየሱስ ሮብ እንዳልተሰቀለ ማስረጃው ይህ ነው

እነዚህ ኢየሱስ ሮብ ተሰቀለ የሚሉ ሰዎች እንዳሉት ኢየሱስ ሮብ ከተሰቀለ እና ሐሙስ እነሱ እንደሚሉት ሰንበት ከሆነ: እነዛ ኢየሱስን ሊቀቡ ሽቶ አዘጋጅተው የሄዱ ሴቶች ሽቶውን ማዘጋጀት የጀመሩት ኢየሱስ ተሰቅሎ የተቀበረ እለት እንደሆነ መፅሐፍ ቅዱስ ይናገራል:: ከእዛም ሀሙስ ሰንበት ነበረ የሚሉት ሰዎች እነዚህ ሴቶች ሐሙስ በሰንበት አረፉ ከእዛ አርብ ቀን ወደመቃብር ሄዱ ማለት ነው እንደእነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ:: መፅሐፍ ቅዱስ ግን እነዚህ ሴቶች የሄዱት እሁድ በሳምንቱ መጀመርያ ቀን እንደሆነ ነው የሚነግረን:: ስለዚህ የእነዚህ ሰዎች መረዳት ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ የስህተት መረዳት መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን::

ሉቃ 23:50 - 56 "እነሆም፥ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤  ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤  አውርዶም በተልባ እግር ልብስ ከፈነው፥ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም ሊጀምር ነበረ። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።"

በመጨረሻም እንደመፅሐፍ ቅዱስ መሠረት በአጭሩ ልመልስ...

ሦስተኛው ቀን --  the third day --  3 day and 3 night  --  ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑን --  ከሦስት ቀንም በኋላ ---  በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ --   በሦስተኛውም ቀን

እነዚህ ሁሉ አንድ አይነት አባባል ናቸው ስለዚህ --  ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑን --  የሚለው አባባል 72 ሰዓት ማለት አይደለም ነገር ግን 72 ሰዓት ነው ብለን ካሳብን የቆርኔሊዎስን ታሪክ በሐዋርያት ሥራ ላይ ከላይ እንዳነበብነው አራተኛው ቀን ማለት ነው

ስለዚህ ኢየሱስ በመዘጋጃው ቀን አርብ ተሰቀለና ሞተ ተቀበረ --- አንደኛው ቀን
ኢየሱስ በሰንበት ቀን በመቃብር ውስጥ ነበር --- ሁለተኛ ቀን
ኢየሱስ እሁድ ማለዳ ከሞት ተነሳ --- ሶስተኛ ቀን


ይህ ነው እንደመፅሐፍ ቅዱስ የሆነ ትክክለኛ መረዳት