Tuesday, January 27, 2015

ሰዎች መንፈሳዊ መንፃት የሚያገኙት እንዴት ነው??

 
ሰዎች መንፈሳዊ መንፃት የሚያገኙት እንዴት ነው??

በሥጋዊው አለም መንፃት የሚካሄደው በውሃ በመታጠብ ነው:: ስለዚህ አንድ ሰው ለመንፃት በውሃ መታጠብ አለበት:: እንግዲህ የመንፈሳዊውም ነገር ለመግለፅ ሁልጊዜ የምንጠቀመው በሥጋዊ አለም በምንጠቀምበት መረዳት ስለሆነ: እንዲሁ እንደነፃን ለመናገር በመንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል: እንዲሁም በቃሉ አማካኝነት በውኃ ታጥባችሁዋል: ነጽታችሁል  የሚል ፅሁፍ ወይም አገላለፅ እናነባለን::

ስለዚህ ውሃ የሚል ባየን ቁጥር የውሃ ጥምቀት የሚል ነገር ሁልጊዜ የሚታሰበን ከሆነ
በውሃ ታጥባችሁዋል የሚል ባየን ቁጥር የውሃ ጥምቀት የሚታሰበን ከሆነ

ወደስህተት መረዳት እንገባለን::

አንድ ሰው ዳግም ከመወለዱ አስቀድሞ በቃሉ መንጻት አለበት:: በመንፈሳዊ አነጋገር በቃሉ መንፃት ማለት በሃጥያአት ምክንያት የጨቀየው ሕይወቱ ከቃሉ የተነሳ መንጻት ይቅር መባል ማለት ነው::

ይኽ የሚሆነው አንዴት ነው??

ይኽ የሚሆነው መጀመርያ አንድ ሰው የእግዝአብሔርን ቃል መስማት አለበት: የእግዝአብሔር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሃጥያአትህ ሞቶልሃል ዋጋ ከፍሎልሃል:: ስለዚህ ከአንተ የሚጠበቀው ይህን ፀጋ በእምነት እንድትቀበል ነው:: ንስሃ እንድትገባ ነው:: የሚለውን መልዕክት ሰምቶ ሲቀበል እና በልቡ ሲያምን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወቱ ጌታ አድርጎ ሲቀበል ያኔ መንፈሳዊ መንፃት: የሃጥያአት ይቅርታ ማግኘት ወይም በሥጋዊ አገላለፅ በውሃ መታጠብ ይሆንለታል:: ልብ ማለት ያለብን በአዲስ ኪዳን ነገሮች መንፈሳዊ ናቸው:: ለምሳሌ የልብ መገረዝ ነው እንጂ ከእኛ የሚጠበቀው የሥጋ መገረዝ አይደለም:: እንዲሁም ለእግዝአብሔር ስግደት በመንፈስና በእውነት እንጂ በሥጋ ጉልበታችን መሬት ላይ መንበርከክ አይደለም: ወዘተ... ስለዚህ ልክ እንደብሉይ ኪዳን ጊዜ በውሃ በመታጠብ መንፃት ሳይሆን መንፈሳዊ መንፃት ነው ከእኛ የሚጠበቀው::

 1 ቆሮ 6:9-11 አብረን እንየው... "ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።"

እዚህ ጋር በግልፅ እንደምናየው በተለያዩ ሃጥያአቶች የቆሸሹ ዓመፆኞችን ከጠራ በሁዋላ እነዚህ የቆሸሹ ዓመፆኞች የእግዝአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ብሎ ይነግረናል:: ከእዛም የዳኑትን እናንተም እንደነዚህ ነበራችሁ ይላል:: አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል ይላል። ይህ ማለት የቆሸሹት ዓመፆች አሁን ነጽተዋል:: ስለዚህ ወደ እግዝአብሔር መንግሥት መግባት ይችላሉ:: ይህ እንግዲህ ከቃሉ የተነሳ የሚደረግ መንፈሳዊ መንፃት እንጂ: ስለውሃ ጥምቀት የሚናገር አይደለም:: ምክንያቱም የሃጥያአት መንፃት የሚገኘው በኢየሱስ ደም ብቻ ነውና::

 ኤፌ 5:25-26 "ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ That he might sanctify and cleanse it with the washing of water by the word,"

እዚህም ጋር በውሃ መታጠብን በመግለጫነት ቢጠቀምም: የውሃ መታጠቡ ግን በቁሳዊ ውሃ መታጠብ ሳይሆን: ከቃሉ የተነሳ ስለሚሆንል መታጠብ ወይም መንፈሳዊ መንፃት የሚናገር ነው:: ምንም ስለጥምቀት የሚናገር አይደለም:: ሁላችንም እንደምናውቀው ጥምቀት የውሃ መታጠብ ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ተቀብረን ከትንሣኤው ጋር መነሳታችንን ከእሱ ጋር መተባበራችንን ለአለም የምናውጅበት ነው::

ዮሐ 15:3 "እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤"

እዚህ ጥቅስ ላይ ስለመንፃት ይናገራል በግልፅ እንደሚናገረው የነፁት በቃሉ ነው

 እዚህ ድረስ ከተግባባን ወደዮሐ 3:5 "ውሃና መንፈስ" የሚለውን ለማስረዳት ልሞክር...

መጀመርያ ዳግም መወለድ ወይም ድነት የሚገኘው እንዴት እንደሆነ ከአጠቃላይ የአዲስ ኪዳን ትምህርት የምንረዳው በእምነት ነው:: አንዳንዶች መልካም ሥራስ ማለታችሁ አይቀርም:: እንደእግዝአብሔር ቃል ከሆነ ግን መልካም ሥራ የድነት ውጤት እንጂ ለመዳን ብለን የምንጥረው አይደለም:: እዚህ ጋር አንድ ሰው ካመነ በሁዋላ እንደፈለገ ሃጥያአት እየሰራ መኖር ይችላል እያልኩ አይደለም:: የእውነተኛ እምነት ፍሬ መልካም ሥራ ብቻ ነው:: ስለዚህ አንድ ሰው እውነተኛ ድነት ወይም እምነት እንዳመነ የሚታወቀው በፍሬው ወይም በመልካም ሥራው ነው::

በጌታ እንድንፈፅማቸው የታዘዝነው ስርአቶች አሉ:: ለምሳሌ ጥምቀት: የጌታ እራት: የመሳሰሉት:: እነዚህ ነገሮች አንድ አምኖ የዳነ ሰው የሚፈፅማቸው ስርአቶች ናቸው::

እንግዲህ ጥምቀት አንድ ሰው አምኖ ከዳነ ወይም ዳግም ከተወለደ በሁዋላ የሚፈፅመው ስርአት ከሆነ: በዮሐ 3:5 ላይ "ውሃ" የሚል ቃል ስለተገለፀ: የሚያሳየው የውሃ ጥምቀት ነው ማለት: ወደተሳሳተ መረዳት ነው የሚወስደን:: ሌላ ቦታ ላይ ስለመወለድ የተገለፀበት ቦታ አለ:: እሱን ማየት ይበልጥ ዮሐ 3:5 እንድንረዳው ይረዳናል እስቲ እንየው...
1 ጴጥ 1:23 "ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።"

እዚህ የጴጥሮስ መልእክት ላይ ስለዳግም መወለድ ሲናገር የተወለድነው በእግዝአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር እንደሆነ ይነግረናል እንጂ ስለጥምቀት በጭራሽ አይናገርም::

ያዕ 1:18"ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።"

እዚህም በያዕቆብ መልእክት ላይ የተወለድነው በእውነት ቃል እንጂ በፍፁም ስለጥምቀት አይናገርም::
ቲቶ 3:5 "እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤"

እዚህም ጋር ስለአዲስ ልደት ወይም ስለዳግም ልደት ይናገራል:: በእዚህም አዲስ ልደት ለማግኘት ከእኛ ምንም አይነት ሥራ እንደማይጠበቅ ነው የሚነግረን:: ከላይ እንዳየነው መንፈሳዊ መንፃት በሥጋዊ አገላለጽ ሲነገር ወይም ሲገለፅ በውሃ መታጠብን ስለሚጠቀም: እዚህም ጋር በውሃ መታጠብ የሚገልፀው መንፈሳዊ መንፃትን ነው:: መንፈሳዊ መንፃትን የምናገኘው ደግሞ በቃሉ ነው:: ቃሉም የሚነግረን ከምህረቱ የተነሣ የተሰጠንን ፀጋ ነው:: ፀጋው ደግሞ እኛ ሃጥያአተኞች የነበረን ሞት የሚገባን: ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሞተልን ደሙን አፈሰሰልን:: የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከሃጥያአት ሁሉ ያነፃል ነው:: ስለዚህ በእዚህም መሠረት ቃሉን አምነን ንስሃ ስንገባ መንፈሳዊ መንፃት ወይም የሃጥያአት ይቅርታ እናገኛለን:: ከእዛም በመንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን::

እዚህም ቦታ ምንም ስለውሃ ጥምቀት የሚናገር ነገር የለም::

መንፈሳዊ መንፃት በትክክል ከገባን ውሃ ባየን ቁጥር ወይም መታጠብ የሚል ባየን ቁጥር የውሃ ጥምቀት ነው እያልን ወደተሳሳተ መረዳት አንገባም
እንግዲህ እስካሁን ከላይ የተናገርኩት ስለመንፈሳዊ መንጻት (የሃጥያአት ይቅርታ) በሥጋዊ አነጋገር ወይም አገላለፅ መታጠብ ወይም በውሃ መታጠብ ከገባን: በዮሐ 3:5 ላይ የተገለፀው "ውሃ" የሚያሳየን ከቃሉ የተነሳ በደሙ ስለሚሆንልን መንፈሳዊ መንፃት ነው::

ከአጠቃላይ የመፅሐፍ ቅዱስ አዲስ ኪዳን ሐሳብ ስንነሳ: ድነት የሚገኘው በሥራ አይደለም:: ወይም ስርዐትን በመፈፀም አይደለም:: ስለዚህ በዮሐ 3:5 ላይ ስለዳግም መወለድ ወይም ስለድነት የሚናገረው ላይ "ውሃ" የሚገልፀው ጥምቀትን ነው ካልን: ጥምቀት ያድናል ወደሚል በጣም ወደተሳሳተ መረዳት ውስጥ እንገባለን:: የኢየሱስን ደም ወደማቃለል የእግዝአብሔርን ፀጋ ወደመናቅ እንገባለን:: ነገር ግን ድነት በእምነት ብቻ ነው: መልካም ሥራም ቢሆን ስርአት መፈፀም: የድነታችን ውጤት ነው:: ብለን ልክ እንደቃሉ ካመንንን ግን: በዮሐ 3:5 ላይ ያለውን "ውሃ" የሚለውን ቃል ጥምቀት ነው ብለን አንረዳውም ምክንያቱም ከቃሉ ጋር እንስማማለን እንጂ አንጋጭም::
ጥምቀት ወይም ሥራ ለድነት እንደማያስፈል ከላይ ተናግርያለሁ:: እሱም የሚደግፍ ግልፅ የሆነ የእግዝአብሔር ቃል ጠቅሻለሁ::

ኤፌ 2:8-9 "ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።"

የሚለውን: ስለዚህ አካራካሪ የሆኑ ቦታዎችን ስንተረጉም: እዚህ በኤፌሶን መልዕክት የተነገረውን ግልፅ ጥቅስ ተደግፈን: አከራካሪዎቹን ለመተርጎም እንሄዳለን እንጂ: ከእግዝአብሔር ቃል ጋር በሚጋጭ ሁኔታ አንተረጉምም::

በእዚህም መረዳት ጥምቀት ለድነት ያስፈልጋል የሚሉ ሰዎች ገላትያን 3:27 ይጠቅሳሉ:: እስቲ አብረን እንየው...

"ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።"

በመጀመርያ ይኼን ወደመተርጎም ከመግባታችን በፊት ከእዚህ ጥቅስ በፊት ያለውን ቁጥር 26 እንየው...

"በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤" ይላል

ስለዚህ ቁጥር 27 ላይ ጥምቀት የሚለውን ከመናገሩ በፊት በእምነት በኩል የእግዝአብሔር ልጆች ሆነዋል:: ያመነ እና የእግዝአብሔር ልጅ የሆነ ደግሞ የጥምቀትን ሥርአት ይፈፅማል:: ስለዚህ እዚህ ቦታ የተጠቀሰው ጥምቀት ለድነት አስፈላጊ ስለመሆኑ አይናገርም::

ይበልጥ ደግሞ እንየው እስቲ...

እዚህ ቦታ ላይ የሚናገረው "ጥምቀት" የውሃ ጥምቀት መሆኑን በምን እርግጠኞች እንሆናለን?? አንዳንድ ሰዎች "አንዲት ጥምቀት" እያለ የእግዝአብሔር ቃል ስለሚናገር: ይህ እዚህ ቦታ ላይ የተጠቀሰው "ጥምቀት" ውሃን ባይጠቅስም የውሃ ጥምቀት ነው ልትሉ ትችላላችሁ:: ትክክል ናችሁ: "የውሃ ጥምቀት" አንድ ብቻ ነው:: ነገር ግን "ጥምቀት" መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የውሃ ጥምቀት ብቻ አይደለም:: እስቲ ይኼን ጥቅስ እንየው...

ዕብ 6:1-2 "ስለዚህ የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ እንሂድ፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፥ እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሐና በእግዚአብሔር እምነት፥ #ስለ_ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው።"

እዚህ ቃል ላይ የሚናገረው ስለ አንድ ጥምቀት ሳይሆን ከአንድ በላይ ስለሆኑ ጥምቀቶች ነው:: ስለዚህ ጥምቀት የሚል ባየን ቁጥር የውሃ ጥምቀት ነው ካልን: ወደስህተት መረዳት ነው የምንገባው::

አሁን የገላ 3:27 "ጥምቀት" ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት ሌላ አንድ ጥቅስ ልጨምር...

1ቆሮ 12:12-13 "አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን #በአንድ_መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን #ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።"

እዚህ ጥቅስ ላይ ስለመጠመቅ ይነግረናል:: የምንጠመቀው ደግሞ በውሃ ሳይሆን #በመንፈስ እንደሆነ ይነግረናል:: ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር አንድ አካል እንድንሆን ወይም ክርስቶስን እንድንለብሰው የተጠመቅነው በውሃ ሳይሆን በመንፈስ (መንፈስ ቅዱስ) ነው::

ይህ በደንብ ከገባን በገላ 3:27 "ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።" የሚለው የተጠቀሰው ጥምቀት: የውሃ ጥምቀት ሳይሆን ስናምን የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ስለምንሆን በመንፈስ ቅዱስ የሚሆንልንን የሚያሳይ ጥምቀት እንደሆነ በቀላሉ እንረዳለን::

ደግሞ የእግዝአብሔር ልጆች መሆናችን የሚመሰክርልንም ሆነ የምንታተምበት በመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ በውሃ ጥምቀት አይደለም::

ኤፌ 1:13-14 " እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።"

ሮሜ 8:16 "የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።"

ይኼን ሃሳቤን ለማጠቃለል...

ውሃ ባየን ቁጥር የውሃ ጥምቀት ነው የምንል ከሆነ
ጥምቀት የሚል ባየን ቁጥር የውሃ ጥምቀት ብቻ የሚታየን ከሆነ

አሁንም ወደተሳሳተ መረዳት መግባታችን ነው:: ስለዚህ የተፃፈውን ስንረዳ: ከአጠቃላይ የእግዝአብሔር ሃሳብ መሠረት ከቃሉ ጋር ሳንጋጭ ለመረዳት እንሞክር::

No comments:

Post a Comment