Monday, July 16, 2012

ለክብሩ ቀናተኛ አምላክ By John Mohammed



                                                                                                                                   በዮሐንስ መሐመድ
                                                            
በስነ-መለኮቱ ዓለም እግዚአብሔር ነገሮችን የሚሠራበት ምክንያት እና መኻከለኛ የሆነው የእርሱ ባህርይ ብዙ አመለካከቶችን ያስተናግዳሉ። አንዳንዶች የእግዚአብሔር መኻከለኛ ባህርይ ቅድስናው ሲሆን ነገሮችን የሚሠራበት መነሻ ምክንያት ደግሞ ፍቅሩ እንደሆነ ይሞግታሉ። በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች የእግዚአብሔርን መኻከለኛ ባሕርይ ፍቅሩን በማድረግ፣ ለሥራው መነሻ ምክንያት ክብሩን ያስቀምጣሉ። ምንም እንኳ ይህች አጭር መጣጥፍ ይህን ትልቅ ስነ-መለኮታዊ ሙግት ትፈታለች ማለት ባይታሰብም፣ እግዚአብሔር ነገሮችን የሚሠራበት መነሻ ምክንያት የእርሱ ክብር እንደሆነ ለማሳየት በብሉይ ኪዳን የሚገኙትን የእግዚአብሔር አወጃዎችን በማሰስ የበኩሏን ትወጣለች።
በየምስባኮቻችን ከተለመዱት ነገር ግን "ውበት" እንደሚለው ቃል ለፍች አስቸጋሪ ከሆኑት ቃላቶች አንዱ "የእግዚአብሔር ክብር" ነው። በካሪዝማቲክና በጴንጤቆስጤው የክርስትና ክንፍ፣የእግዚአብሔር ክብር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በመግለጥ ከሚሠራቸው የፈውስ፣ የታምራትና ትንቢታዊ ከሆኑ ስጦታዎች ጋር ይያያዛል። ለዚህምክብርህን ግለጥከሚሉት ፀሎቶች በተጨማሪ እነዚህ የእግዚአብሔር ሥራዎች በተገለጡበት ጉባዔ ፍጻሜ የሚስተዋሉትዛሬ የእግዚአብሔር ክብር ተገልጦ ነበርክብሩን መናፍስት ሊቋቋሙት አልቻሉም ነበርየሚሉትና የመሳሰሉት የተለመዱ አስተያየቶች በቂ ምሳሌ ናቸው። በእርግጥ እግዚአብሔር በክብሩ በጉባዔዎቻችን ሲያልፍ መቆም የሚችል ሰይጣንም ሆነ ተቃራኒ ኃይል የለም። እርሱም ከክብሩ የተነሳ ፈውስንም ሆነ የስጋችንን ድካም የማንሳት ሥራን እንደፈቀደ ይሠራል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ክብር በዚህ ብቻ መወሰን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።
ከላይ የተጠቀሱትን አባባሎች ለለመደ አእምሮ የማይዋጥ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱሳችን ከእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ጋር የሚያይዛቸው፣ መልካም ብሎ አእምሮአችን የሚያምንባቸውን ነገሮች ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈሪ ነገሮችንም ጭምር ነው።ክብርህን አሳየኝ”(ዘጸ 3318 )[i] ለሚለው የሙሴ ልመና የተሰጠውማንም እኔን አይቶ መኖር ስለማይችል፣ ፊቴን ማየት አትችልም” (ዘጸ 3320 ) የሚለውን አምላካዊ መልስ፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፊት የማይገባውን እሳት አቅርበው በእግዚአብሔር እሳት ለተበሉትና ሬሳቸው በወንድሞቻቸው ተጐትቶ ሲወጣ ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣ ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከበራለሁ (ዘሌ 103) ያለው ምክንያታዊ የእግዚአብሔር ድምጽ ከእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ጋር ያሉትን አስፈሪ ክስተቶች ከሚገልጡ አያሌ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ጥቂቶቹ ናቸው።  የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በብሉይ ኪዳን የሚገኙትን የእግዚአብሔር እወጃዎች ማሰስ ቢሆንም አዲስ ኪዳንም ይህን እውነት በዝምታ እንደማያልፈው መጠቆም መልካም ነው፡፡ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ለተናገረው ዲስኩር ይህ የአምላክ ድምጽ ነው ተብሎ በሕዝቡ ዘንድ የአምላክን ስፍራ ተችሮት ለተሞካሸው ንጉስ ሄሮድስ የእግዚብሔር ምላሽ የሞት ቅጣት ነበር-ከሞትም በትል ተበልቶ መሞት! ለዚህ ሞት መከሰት መንፈስ ቅዱሰ በቅዱስ ሉቃስ አማካኝነት የሰጠው ምክንያት  ሄሮድስም ለእግዚአብሔር ክብር ስላልሰጠ የጌታ መልአክ ወዲያው መታው፣ በትልም ተበልቶ ሞተ። የሚል ነበር። አነዚህንና የመሳሰሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ስናይ ክብርህን ግለጥፀሎቶቻችን ምላሽ ከክብሩ የተነሳ መርካት (መዝ 1715) ብቻ ሳይሆን ፍርድም ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ልከኛና ሚዛናዊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ነው።
"ክብር" የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙትልዕልና፣ ላቂያ፣ ብልጫ፣ ሹመት፣ ሽልማት፣ ታላቅነት፣ ኀይል ብዕል፤ ብዙ ገንዘብ[ii] ይሉታል። ስለዚህ በጥሬ ቃሉ የእግዚአብሔር ክብር ስንል ገናናነቱን፣ ወደር የለሽነቱን፣ ባለጠግነቱን እንዲሁም በኃይሉና በግርማው እኩያ የለሽ ማንነቱን ነው። ብሉይ ኪዳንም በመጀመሪያ በተጻፈበት  የእብራይስጥ ቋንቋ ክብር ማለትካቦድሲሆን ከባድ፣ ግዙፍ፣የከበረ፣ደማቅ፣የተትረፈረፈ የሚሉትን ትርጉሞች ያዘለ ነው[iii] አዲስ ኪዳንም በተጻፈበት በጽርእ ክብር ማለትዶክሳሲሆን ትርጓሜውም ከእብራይስጡ አቻው እምብዛም አይለይም።  የአማርኛ መዝገበ ቃላቶቻችንም ከዚህ ትርጉም የራቁ አይደሉም።[iv] ከላይ የተሰጡትን ትርጉሞች በግርድፉ እንደሚያሳዩን የእግዚአብሔር ክብር ማንነቱን፣ ባህርያቱንና ከማንነቱ የሚመነጩትን ነገሮች ሁሉ ያጠቃልላል። እነዚህን  ትርጉሞች እሳቤ ውስጥ ካስገባን፣ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ለክብሩ ይሠራል ማለት፣ በእግዚብሔር የተሠራ ነገር ሁሉ የታቀደው ለእግዚአብሔር ከፍ ብሎ መታየት፣ ለስሙ መግነንና አቻ የለሽነቱን ለማወጅ ነው ማለታችን ነው። ይህንንም ዓላማችንን የሚያሳዩትን የእግዚአብሔርን እወጃዎች ከዚህ በመቀጠል እንመለከታለን።
ለክብሩ የሚሠራ አምላክ
በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከተጻፉት ክፍሎች ውስጥ እንደ ኢሳይያስ 489-11 እግዚአብሔር ለሚሠራውን ነገር ሁሉ ምክንያት ክብሩ እንደሆነ ፍርጥ አድርጐ የሚያሳይ ክፍል ማግኘት ያዳግት ይሆናል። እልከኛና ወደ ጣኦት አምልኮ ከእግዚአብሔር ዘወር በማለቷ በእርሱ ትእዛዝ በባቢሎን ተማርካ ለነበረችው እስራኤል ከምርኮ የመመለሱን አዲስ ነገር የሚሠራበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ይገልጻል።
ስለ ስሜ ስል ቁጣዬን አዘገያለሁ፤ ስለ ምስጋናዬ ስል ከአንተ እገታዋለሁ፤ይኸውም እንዳልቆርጥህ ነው። እነሆ፤ እንደ ብር ባይሆንም አንጥሬሃለሁ፤ በመከራ እቶን ፈትኜሃለሁ። ስለ ራሴ፣ ሰለ ራሴ ስል አደርጋለሁ፤ ራሴን ለውርደት እንዴት አሳልፌ እሰጣለሁ? ክብሬን ለማንም አልሰጥም።” ( ኢሳ 489-11)
"ስለ ስሜ" "ስለ ምስጋናዬ" "ስለ ራሴ" "ራሴን ለውርደት እንዴት አሳልፌ እሰጣለሁ" እና "ክብሬን ለማንም አልሰጥም" የሚሉት ሐረጐች በእኔነት ለሰከረው የሰው ልጅ የሞት ፍርድ ያህል የሚከብዱ ናቸው። እግዚአብሔር የእስራኤልን እልከኝነት፣ልበ ድንዳኔና አታላይነትን ( ኢሳ 4848) አስረግጦ በመንገር የሚሰራውን አዳዲስ ነገሮች ( ኢሳ 486) ከእስራኤልም ሆነ ከሚያመልኳቸው ጣዖቶች ( ኢሳ 485) ጋር ሳይሆን ከእርሱ ስም፣ ክብርና ምስጋና ጋር ብቻ ያያይዘዋል። እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያለው ሙግት በአጭሩ ወደነበራችሁበት ስፍራ እናንተን ከምርኮ የምመልስበት ምክንያት ስሜ እንዳይጐድፍ፣ እንዳይዋረድና እንድመሰገን ነው የሚል ነው። ይህለራሴ ስልብቻ አደርጋለሁ የሚለው የእግዚአብሔር መልስ ዋጋን ለማግኘት ወደራሱ ለሚመለከተው የሰው ልጅ የሬትን ያህል  ይመራል። በተለይ በዚህ የሰው ልጅ በማንነቱ እንዲታመንና እንዲኮራ፣ በቤተክርስትያን ውስጥም እኔነት በተሞሉ ዝማሬዎችና ስብከቶች ይኸው እኔነት እየደለበ ባለበት ዘመን ይህ የእግዚአብሔር አዋጅ በብረት በትር ማጅራትን የመመታት ያህል ከባድ ነው።
እርግጠኛ ጊዜውን በትክክል ባላስታውስም፣ ከተወሰኑ አመታት በፊት አንድ የታወቀ ሰባኪ ሰው የተፈጠረበትን ምክንያት ሲናገር ሰምቻለሁ። ሰባኪው እግዚአብሔር የአዳምን ብቸኝነት ለማስወገድ ሔዋንን እንደፈጠረ አስረግጦ በመንገር፣ በተዛማጅ መልኩም የአዳም መፈጠር የእግዚአብሔርን ብቸኝነትንና የህብረት ፍላጐት ለመሙላት እንደሆነ በድፍረት ሲያስረዳ ጉባዔውም ይህንን የድፍረትና የስድብ ቃል በእልልታ እንዳጀበ አስታውሳለሁ። እንደነዚህ አይነት አስተሳሰቦች ሰለ ራሳችን አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን ታስበው የሚነገሩ ቢሆኑም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የራቁ በመሆናቸው ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል ሰውንም እውነተኛ ከሆነው ከእግዚአብሔር አምልኮ ራስን ወደ ማምለክ ይወስዱታል። የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ( ሐዋ 1724) ሲሆን፣ ከሰው ልጅ ጋር ባለው ግንኙነትም ሁል ጊዜ ሰጪ እንጅ ተቀባይ እንዳልሆነ ቅዱስ ጳውሎስ እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም (ሐዋ 1725 ) በማለት የእግዚአብሔርን የአድራጊነት ክብር ያሳየናል። እርሱ ስለራሱና ስለ ስሙ ምስጋና በሚያደርገው ሁሉ ይከበራል ገናናነቱንም ያሳያል። እርሱ ከፍጥረት በፊት በዘላለም የነበረ፣ያለና የሚኖር ስለሆነ ለመኖሩ እኛ አናስፈልገውም።  እርሱ ለዘላለም በሥላሴ ውስጥ ባለው ፍጹም ደስታና ህብረት ( ዮሐ 17 5) የሚኖር በመሆኑ እኛ ከእርሱ ጋር ያለን ህብረት ለእኛ ደስታ ጭማሬ( 1 ዮሐ 14) እንጂ ለእርሱ አይደለም። አዎን እርሱ ሁል ጊዜ ለክብሩ የሚሰራ ብቻውን መወደድና መመለክን የሚፈልግ ኦምላክ ነው።
ፍጥረት ለእግዚአብሔር ክብር
እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከመፍጠሩ በፊት ሌሎችን ፍጥረታት እንደፈጠረ የዘፍጥረት መጽሐፍ ይተርክልናል። የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት በኋላ መፈጠሩ ሌሎች ፍጥረታት ለሰው ልጅ ሲባል እንደ ተፈጠሩ ስነ-መለኮታዊ ትርጉም ለዘፍጥረት መጽሐፍ በመስጠት የሚነግሩን ሰባኪዎች አሉ። በእርግጥ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከመፍጠሩ በፊት ሰው የሚኖርበትን አካባቢ ለሰው ህልውና በሚያስፈልጉ ነገሮች ሞልቶ እንደ ነበረ ዘፍጥረት ይተርክልናል። ለሰው ልጅ የሚያስፈልገው ተስማሚ አየር፣ ለምግብ የሚያስፈልጉት እፅዋእት፣ ቀናትንና ዘመናትን የሚለይበት ብርሃናት እና ከዋክብት፣ በእግዚአብሔር እቅድ ሰው ከመፈጠሩ አስቀድሞ እንደተሰሩ ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ይነግረናል። ይህ የፍጥረት ትረካ ከሚያስነሳቸው አያሌ ስነ-መለኮታዊ ጥያቄዎች አንዱ በፍጥረት ውስጥ አምብርቱ እግዚአብሔር -ወይስ ሰው የሚለው ነው? መልሳችን ሰው የሚለው ከሆነ ሰው ያልደረሰባቸውን ከሰው ጋርም በቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን የሰማይ ከዋክብትን የምድር ፍጥረታትና ሰው አይቶአቸው የማያውቀውን የባህር እንስሳት የመፈጠር ዓላማ ምን እንለዋልን? ሰው እግዚአብሔር በፈጠረለት አካባቢ ላይ በጥገኝነት የሚኖር ባለሥልጣን መሆኑ የፍጥረት መኻከለኛ ያደርገዋልን?
መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉልን ቅዱሳን የሰውን መኻከለኝነት አይጋሩትም። ለእነርሱ የፍጥረትም ሆነ የሁሉም ነገር እምብርት ፈጣሪው እግዚአብሔር ነው። እነዚህን ፍጥረታት ያስተዋለው ዳዊት የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ሰፍራ ትሰጠው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?” (መዝ 83-4 ) በማለት ክብር የሚገባውንና በራሱ ተነሳሽነትና ቸርነት በፍጥረቱ ሁሉ ላይ የማስተዳደር ስልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠውን እግዚአብሔርን ያመሰግናል(መዝ 819)፡፡ በመጨመርም ዳዊት ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤የሰማይም ጠፈር የእጁን ስራ ያውጃሉ (መዝ 191) በማለት ፍጥረት የተፈጠረበት የመጀመሪያ ዓላማ የእግዚአብሔር ክብር እንደ ሆነ ትዕቢትን አስተንፋሽ በሆነው ስነ-መለኮታዊ አስተሳሰብ ይዘምርልናል። መጽሐፍ ቅዱሳዊው አመለካከት አነዚህን ከሰው ይልቅ የገዘፉ የእግዚአብሔር ጣት ስራዎችን ስናይእግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው!” (መዝ 819) ብለን በአምልኮ ወደ እግዚአብሔር እንድንመለከት እንጂ ወደ ራሳችን አይተን ይህ ሁሉ ለእኔ ነው እንድንል አይደለም። ለምን ቢባል? እውነቱ ፍጥረት ለሰው ልጅ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ስለ ሆነ ነው። ጸሐይ ስትወጣና ስትጠልቅ ያለው ውበት ለሰው ልጅ ሊያውጅ የሚገባው የፈጣሪን ክብር ( መዝ 191) እንጅ አምልኮተ ፍጥረትን አይደለም። አዎን እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ የሰራው እርሱ መኻከለኛ ሆኖ እንዲከበርና ገናና ሆኖ እንዲታይ ነው፤ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የሚሰራው ለክብሩ ነውና።
ዘጸአት ለእግዚአብሔር ክብር
እግዚብሔር ሁሉን ነገር ለክብሩ እንደሚሰራ ከሚያሳዩን የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካዎች አንዱ የእስራኤል ከግብጽ የመውጣት ታሪክ ነው። እስራኤላውያን ለብዙ አመታት በባርነት ከቆዩበት የግብጽ ምድር አወጣጣቸው ተአምር ነበር። በግብጽ ምድር የተደረጉት ተአምራቶችና መቅሰፈቶች በአይነታቸው እጅግ የተለዩና በግብጽ አማልክት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ያሳዩ ነበሩ። ይህ ቸር የሆነው እግዚአብሔር ከአስገባሪዎቻቸው በሚደርስባቸው በደል ወደ እርሱ የጮሁትን (ዘጸ 222-24) እስራኤላውያንን ከግብጽ ያወጣበት መንገድና የግብጽ ንጉስ የፈርዖን የልብ ድንዳኔ (ዘጸ 73) እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ሁሉን ቻይ የሆነው እግዚአብሔር እነዚያን ሁሉ መቅሰፍቶች ለምን በግብጽ ላይ ማዝነብ አስፈለገው? ፈረዖንንስ በዚያ ሁሉ የልብ ድንዳኔ እንዲያልፍ ለምን ፈቀደ ? ለምንስ የፈርዖንን ልብ አደነደነው?” (ዘጸ 421)
በእነዚህ ብዙ አሰቃቂ እና አስደናቂ ተአምራቶች ውስጥ የዘጸአት መጽሐፍ ለአንባቢው የሚሰጠው ምላሽ ይህ ነው፤
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሽማምንቱን ልብ አደንድኛለሁና፤ ይኸውም ግብፃውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔንም እንድታውቁ ነው።” (ዘጸ 101-3)
አነዚህ ሁሉ መቅሰፍቶችና ታምራዊ ምልክቶች ያስፈለጉት እግዚአብሔር በቅጽበት እስራኤልን ከግብጽ ማውጣት የሚያቅተው አምላክ ሆኖ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ ያደነደነበት ምክንያት ተዓምራትን በማድረግ የእርሱ ክብርና ብቸኛ አምላክነት ለሚመጣው የእስራኤል ትውልድ እንዲነገር ነው(ዘጸ 101)፡፡ እስራኤል - በፀና የእግዚአብሔረ ክንድ ከግብጽ ከወጣች በኋላ አንኳ ፈርዖን ልቡን አደንድኖ እስራኤልን የተከተለበት ምክንያትን እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ በማለት ነግሮታል
እኔም የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ አግዚአብሔር (ያህዌ)መሆኔን ያውቃሉ።” (ዘጸ 144)
አግዚአብሔር በታሪክ ወስጥ አነዚህን ታምራቶች የሰራበትለራሴ ክብርንአገኛለሁ በሚል ምክንያት ነው። በእርግጥ በራሳችን መልክ የሰራነውንና አኛ እንደፈለግን የምናዘውንአምላክ”( ያስተውሉ ይህ እውነተኛው እምላክ አይደለም) ለምንወድ ሰዎች አነዚህ የእግዚአብሔር እወጃዎች የሚከብዱ ናቸው። ነገር ግን እግዚአብሔር ለክብሩ ሲል የሚሰራቸው ስራዎች እርሱን ለሚወዱት ሁሉ ለመልካም እንደ ሆነ (ሮሜ 828) ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይህ በኃያሉ እግዚአብሔር ፊት በአክብሮት ለመኖር የአምልኮ ምክንያት  ይሆናል። አዎን እግዚአብሔር ታምራትንና ሁሉ ነገር የሚሰራው እርሱ መኻከለኛ ሆኖ እንዲከበርና ገናና ሆኖ እንዲታይ ነው፤ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የሚሰራው ለክብሩ ነውና።
የእስራኤል መበተንና መሰብሰብ
እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጽ ካወጣ በኋላ ለእስራኤል በሰጠው ቃል ኪዳን ውስጥ የጣዖትን እምልኮ ወይንም ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር ለሌላ መስጠትን (ዘጸ 203-6) እጅግ እንደሚጠላ በብዙ ቃል ተናግሯቸዋል። በዙሪያቸው ያሉትን ሀገራት ጣዖታት ቢያመልኩ የሚመጣባቸው እርግማን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በምርኮ መወሰድና መበተን እንደሆነ በግልጽ ተነግሯቸዋል(ዘዳ 2862-64)፡፡ የእስራኤልም ህዝብ እግዚአብሔር የገባለትን ተስፋ ከወረሰ በኋላ ብቻውን መመለክና ክብሩን የሚወደውን እግዚአብሔርን ትቶ በዙሪያው ያሉትን የተለያዩ ሀገራት አማልክት ሲያመልክ ቃሉን ከሚጠብቅ እግዚአብሔር ዘንድ መበተን ለእስራኤል ህዝብ ዕጣው ሆነ። ሰለ መበተናቸውም እግዚአብሔርም ስለ እስራኤላውያን አኗኗር ሲናገር እንዲህ አለ
ስለዚህ በምድሪቱ ላይ ደም ስላፈሰሱና በጣዖታቶቻቸው ስላረከሷት፣ መዓቴን አፈሰስሁባቸው። በአሕዛብ መካከል በተንኋቸው፤ እነርሱም በየአገሩ ተበታተኑ፤አንደ ጠባያቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው። በአሕዛብ መካከል በሄዱበት ሁሉ ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤” (ሕዝ 3618-20)
እግዚአብሔር የተለያዩ አሕዛብ ነገስታትን በመጠቀም እስራኤላውያንን ስለ ጣዖታት አምልኮና ህግን ስለ መጣስ በተናቸው። ለዚህ ሁሉ መሰረታዊ ምክንያት በቅድስና ባለመኖርና የእግዚአብሔርን ክብር ለጣዖታት በመስጠት የእግዚአብሔርን ቅዱስ ስም ማርከሳቸው ነው። ለክብሩ ቀናተኛ የሆነው አምላክ ይህን በዝምታ አላየውም። በአሕዛብ መካከል በተናቸው ለቃሉም ታማኝነቱን አሳየ።  አዎ ብቻውን መከበርና መወደድ የሚፈልግ አምላክ ነውና። ክብሩ ለሌላ ሲሰጥ እስራኤልን በተነ፡፡ሰለ ጣዖታት አምልኮ እስራኤልንም ሲገስጽ እንዲህ አለ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።” (ኢሳ 428)
እግዚአብሔር ምንም እንኳ በቃሉ ውስጥ እስራኤላውያን ከጣኦት አምልኮአቸው ወደ እርሱ ቢመለሱ ተመልሶ እንደሚሰበስባቸው ተስፋ ቢሰጣቸውም (ዘዳ 301-3) ለመሰብሰብ ስራው ምስጋናውን ለእነርሱ አልሰጠም። በነቢዩ ሕዝቅኤል መጽሐፍ እንዲህ በማለት እግዚአብሔር ክብሩን ይወስዳል
የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ይህን ሁሉ የማደርገው ስለ እናንተ ብዬ ሳይሆን፣ በየሄዳችሁባቸው አሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ነው። በአሕዛብ መካከል የረከሰውን፣ እናንተ በእነርሱ ዘንድ ያረከሳችሁትን፣ የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ፤ ከዚያም ዐይኖቻቸው እያዩ፣ በእናንተ አማካይነት ራሴን ቅዱስ አድርጌ ስገልጥ፣ አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ሕዝ 362223
እግዚአብሔር ለእስራኤል ይህንን አልሸሸገም የሚሰበስባቸው ስለ እነርሱ ብሎ ሳይሆን አሁንም ስለ ስሙ አሕዛብም እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ እንዲያውቁ ነው። በእርግጥ እርሱ ፍጥረትን፣ ታላላቅ ነገሮችን፣ እስራኤልንም መበተንና መሰብሰብ ለራሱ ክብር የሚሰራ አምላክ ነው።
አንግዲህ ምን ይሁን?
ይህ ጽሑፍ ያጠቃለላቸው ጥቂት የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች፣ እግዚአብሔር የሚሰራውን ሁሉ ለምን ይሰራል የሚለውን ጥያቄ ለክብሩ፣ለስሙ፣ ለራሱና አምላክነቱን ለማሳየት በሚሉ መልሶች የተሞሉ ናቸው። ይህንንም በብሉይ ኪዳን ትረካ ውስጥ ቁልፍ ታሪኮች ከሆኑት ከፍጥረት ከዘጸአትና ከምርኮ ታሪክ አይተናል። አሁን በዚህ ዘመን ለምኖረው ሰዎች ይህ ምን ይፈይድልናል? የአዲስ ኪዳን መጸሐፍትስ ከዚህ የተለየ እውነት አላቸውን? ይህስ እውነት በሕይወታችን ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? የህንን በሚቀጥለው እስክንመለስበት ድረስ አሁንከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አለን? ፈጽሞ! ወይም ሌላ ዐለት አለ? የለም! ማንንም አላውቅም።ያለውን ብቻውን ክብርና ምስጋና የሚገባውን ኦምላክ እናምልክ፣ ለእርሱም እንኑር ለስሙ የሚገባውንም ክብር እንስጥ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ አንተ ብቻህን ያለህ ሁሉን ለክብርህ የምትሰራ አምላክ ነህ! ላደረግከውና ለምታደርገው ሁሉ ክብር ለአንተ ይሁን። Soli Deo Gloria!


[i] በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ያሉት ጥቅሶች ሁሉ የተወሰዱት 1993 . ከታተመው አዲሱ መደበኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
[ii] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ስዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ( አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ፣ 1948 . .) ገጽ፣519
[iii] F. Brown, S. Driver and C. Briggs (BDB), The Brown-Driver-Briggs Hebrew and English Lexicon ( Massachusetts: Hendrickson Publishers, 2006), 457-8
[iv] ከኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት በተጨማሪ የደስታ ተክለ ወልድ፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ( አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ፣ 1962 . .)፣ገጽ፣ 636 ይመልከቱ።

No comments:

Post a Comment